ረቂቅ አዋጁ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች የይዞታ ዋስትናን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተጠቆመ

ረቂቅ አዋጁ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች የይዞታ ዋስትናን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጥር 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጁ የአርሶና አርብቶ አደሮች የይዞታ ዋስትናዎችን በማረጋገጥ፣ በይዞታቸው የመጠቀምና ባፈሩት ንብረት የፋይናንስ ብድር ማግኘት መብት የሚያረጋግጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

አዋጁ የሴቶችን እና የመንግስት ሰራተኞችን የይዞታ ባለቤትነት መብት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከፍትህ ተቋማት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ከተውጣጡ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አድርጓል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ መድረኩ የተዘጋጀበትን ምክንያት ምክር ቤቱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 7/2016 ዓ.ም መርምሮ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በተባባሪነት ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን አስታውሰው ረቂቅ አዋጁ ከተመራ በኋላ ሁለቱም ቋሚ ኮሚቴዎች በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ መምከራቸውን አብራርተዋል።

በቀጣይም በክልሎች የአርሶና አርብቶ አደሮችን ተሳትፎ ትኩረት በማድረግ የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮችን በማዘጋጀትና ግብዓቱን በማካተት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ በማቅረብ የሚፀድቅ መሆኑን አብራርተዋል።

ሰብሳቢው አያይዘውም ረቂቅ አዋጁ የይዞታ ምዝገባ መረጃ ስርዓትን የሚዘረጋና ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማገዝ የመሬት ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ለአገራችን ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ሀላፊ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በመድረኩ ላይ በቂ ግብዓት እንደተገኘና ከሕዝብ የተነሱት ጥያቄዎችም ተካተው በአግባቡ ቀጣይ በቂ ምላሽ እንደሚያገኙ አስገንዝበው፣ ለግብርና የተሰጠው አገራዊ ተልዕኮ ግብርናን በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴታው አያይዘውም ዋናው ወሳኝ ጉዳይ የመሬት አጠቃቀማችን በዘፈቀ ስለሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በአገራችን ባለመኖሩ የአካባቢ መራቆትን፣ የደን መጨፍጨፍን፣ የአፈር መሸርሽርን እና የአየር ንብረት የሚያስከትለውን ችግር ለመቀነስ ረቂቅ አዋጁ ያግዛል ብለዋል።

መታረስ የማይገባቸው መሬቶች እየታረሱ ስለሆነ ለአርሶ አደሮች አማራጭ የህልውና መሰረት በመስጠት መሬቱ እንዲያገግም እድል ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበው፣ አጠቃላይ ሁሉንም ተቋማት ያካተተ ፖሊሲ እስኪወጣ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የበረሃማነት አደጋ ስጋት ያጋጥማል ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

በግብርና ሚኒስቴር የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተካተቱ ለውጦች መካከል የይዞታ ማረጋገጫ የምስክርነት ወረቀትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ፣ የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ፣ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት፣ የሴቶችና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሬት የመሸጥም መብት እና ሌሎችም እንዳሉ አብራርተዋል።

የህግ ባለሙያው አክለውም ረቂቅ አዋጁ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑና አዋጁ የማዕቀፍ ህግ መሆኑንና ዝርዝር ጉዳይችን አለመያዙን ግምት ውስጥ መግባት ካለባቸው መሰረታዊ ነጥቦች መሆናቸውን አስረድተው፣ ዋናው ዓላማው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ምንጭ ፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት