የኢሲፔ ዲቻ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎፋ ዞን ኢሲፔ ዲቻ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ከግብይትና ግበዓት አቅርቦት እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች ከ1 ሚሊዮን 300 ሺ ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡ ገልጿል።
ኅብረት ሥራ ዩኒዬኑ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር ጠቅላላ አመታዊ ጉባኤ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ኢሲፔ ዲቻ ኅብረት ሥራ ዩኒዬን በ2000 ዓ.ም በ13 መሠረታዊ ማህበራት፣ ከ65 ሺህ ብር በማይበልጥ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን ዛሬ በስሩ ያሉ ማህበራትን ቁጥር 56 በማድረስ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳስመዘገበ የዞኑ ኅብረት ሥራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አማረች በየነ ገልፀዋል።
በጉባኤው የተገኙ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በበኩላቸው ኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለአርሶ አደሩ የተሻለ ትርፍ የሚያስገኙ የገበያ ሰንሰለቶችን ከመዘርጋት ባለፈ የግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የዋጋ ንረት ከማስተካከል አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለቸው አንስተዋል።
የኢሲፔ ዲቻ ኅብረት ሥራ ዩኒዬንም ከተመሠረተ ጀምሮ የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያመላከቱት አስተዳዳሪው በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኅብረት ስራ ዩኒዬኑ ጠቅላላ እንቅስቃሴ፣ የኦዲትና የዘንድሮው አመት ቀጣይ እቅድ ሪፖርቶች ሰነድ ለአባላቱ ቀርቧል።
የግዥ ክፍያ ስርአቱ ህጋዊ ሂደትን ተከትሎ አለመፈጸም በጠቅላላ ትርፍ ላይ ያሳረፈው ጫና፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለይቶ ግዥ አለመፈፀምና የስራ ማስኬጃ ወጪዎችን አልፎ አልፎ ያለ ውሳኔ መጠቀም በኦዲት ግኝቱ የተካተቱ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።
የጎፋ ዞን ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ እስጢፋኖስ ከግብይትና ግበዓት፣ ከኬሚካል አቅርቦትና ከሌሎች አገልግሎት ዘርፎች ከ1ሚሊዮን 300ሺህ ብር በላይ የተጣራ ትርፍ መገኘቱን ገልጸዋል።
ለዘንድሮው የምርት ዘመንም በቂ የግበዓትና ምርጥ ዘር ክምችትን ጨምሮ ከእህል ግብይት ሂደት የሻለ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በቀረበው ሰነድ መነሻ በአባላቱ ውይይት የተደረገ ሲሆን ባጋጠሙ ችግሮችና ቀጣይ መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
የአክሲዮን ሽያጭ መነሻ ዋጋን 10 ሺህ ብር ለማድረስና የውስጥ ሰራተኛን ወርሃዊ ደሞዝ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ ሀሳብ አባላቱ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ በስራ ዘመኑ የተሻለ አስተዋፆ ላበረከቱ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ