ካለፈው ስህተት ተምረን ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጀን ነው – የኮሬ ዞን የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችና መምህራን

ካለፈው ስህተት ተምረን ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጀን ነው – የኮሬ ዞን የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችና መምህራን

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ካለፈው ስህተት ተምረን ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጀን ነው ሲሉ የኮሬ ዞን የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችና መምህራን ገለጹ፡፡

ተማሪ እሱባለው ዘማች፣ ሚሊያና ሞገስና ሌሎችም በኬሌ፣ ቆቦ እና ሲንግ ኬላ ትምህርት ቤት ከሚገኙ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ሲሆኑ አምና ላይ በየትምህርት ቤታቸው የተሠራው የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት ዝቅተኛ እንደነበር ነው የተናገሩት።

ዘንድሮ ላይ ደግሞ ካለፈው ስህተት በመማር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመዘጋጀት ላይ እንዳሉና መምህራኑም በሚችሉት አቅም እያዘጋጁንና እውቀት እያስጨበጡን ይገኛሉ ብለዋል።

መምህር ጌትነት ገነነ፣ ደሳለኝ ተስፋዬ እና ሌሎችም በኬሌ፣ ቆቦ እና ሲንግ ኬላ ትምህርት ቤት ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል ሲሆኑ አምና በየትምህርት ቤታቸው የተገኘው ውጤት አነስተኛ እንደነበር አንስተዋል።

የአምናውን የውጤት ስብራት ለማከም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ያሉት መምህራኑ ዘንድሮ በተማሪዎችም ላይ ጥሩ ቁጭትና መነሳሳት እንዳለ ጠቁመው እኛም የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን ነው ያሉት።

ካነጋገርናቸው ርዕሳነ መምህራን መካከል የኬሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ስዩም ተካራ እና የሲንግ ኬላ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አጋፋሪ አዶሸ የአምናው ውጤት እንዳይደገም የነበሩብንን ድክመቶችና ክፍተቶችን ለይተን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተማሪዎችን እየተከታተልንና መምህራንም በአግባቡ እንዲያስተምሩ እየሠራን ነው ብለዋል።

የኮሬ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አያለው አሳምነው የወላጆች ክትትልና ድጋፍ ማነስ፣ የተማሪዎች ትኩረትና ፍላጎት መቀነስ፣ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ የመጽሐፍት ዕጥረትና የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ድክመት ለውጤት ስብራት በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆኑ ነው የተናገሩት።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የነበሩ ክፍተቶችን ለይቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ወደ ሥራ ገብተናል ያሉት አቶ አያሌው ሁሉም የድርሻውን ከተወጣና ተማሪዎችም ትኩረት ሰጥተው ከተማሩ ጥሩ ውጤት የማይመጣበት ምክንያት የለም ብለዋል።

ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን