የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ“ድሽታ ግና” በዓል በአደባባይ መከበሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ“ድሽታ ግና” በዓል በአደባባይ መከበሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ“ድሽታ ግና” በዓል በአደባባይ መከበሩ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጎልበት፣ የተጣላ ግለሰብም ይሁን ህዝብ በማስታረቅ ለልማት ህዝብ እንዲዘጋጅ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጨወት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ገልጸዋል፡፡

የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ድሽታ ግና” በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

ለአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ“ድሽታ ግና” በዓል ታዳሚ እንግዶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአሪ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በዓሉ ዘንድሮ በአደባባይ ሲከበር ለ8ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው “ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሄ” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“ድሽታ ግና” የዘመን መለወጫ በዓል ከመሆን ባሻገር ለሰላም፣ አንድነት፣ ብልፅግናና ለሀገር ግንባታ ካለው ፋይዳ አኳያ መንግስት የበዓሉ እሴቶች እንዲጎለብቱ በልዩ ሁኔታ እንዲከበር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በተለይም በአደባባይ መከበሩ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጎልበት የተጣላ ግለሰብም ይሁን ህዝብ በማስታረቅ ለልማት ህዝብ እንዲዘጋጅ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት አስተዳዳሪው፡፡

የ“ድሽታ ግና” ዘመን መለወጫ በዓል ከባዱ የረሃብ የዝናብና ውጣ ውረድ ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት በደረሱ እሸቶች በአረንጓዴ ለምለም መስክ በልጅአገረዶች ጨዋታ የአሪ ብሔረሰብ የሚቀበሉት በዓል ነው ብለዋል፡፡

“ድሽታ ግና”ን ለማክበር በየአካባቢው የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት፣ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ በየቤቱ አዳዲስ የሚቀመሱ ምርቶች የሚወጣበት ወቅት ሲሆን የተዘሩ ሰብሎች ለፍሬ ሲበቁበትና የሚረቡ ላሞች ወተት ሲሰጡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነውን ፈጣሪ በ“ድሽታ ግና” በዓል ይመሰገናል፡፡ በክፉ ቀንም የደረሱ ሰዎች በዚሁ በዓል ይመረቃሉ ይመሰገናሉ፡፡

በብሄረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የአሪ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ “ድሽታ ግና” በዓል እሴቶችን ይበልጥ ለማጎልበትና ሀገራዊ ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና በሚጠቅም መንገድ ጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉ አለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግና በዮኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገብ ለማድረግ ዞኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

በዓሉ የሰላም የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በበዓሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ እና የዕለቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ አለማየሁ ባውዲ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ጸሀይ ወራሳ፣ የክልሉ የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አዳማ ትንጳዬ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ፣ የአዲስ አበባ የባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።

አዘጋጅ፡ ብዙነሽ ዘውዱ