ከጎፋ እና ከባስኬቶ ዞኖች ከ179 ሚሊየን ብር በላይ የጡረታ መዋጮ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ነው – በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሣውላ ቅ/ጽ/ቤት
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከጎፋ እና ከባስኬቶ ዞኖች ከ179 ሚሊየን ብር በላይ የጡረታ መዋጮ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሣውላ ቅ/ጽ/ቤት አስታወቀ።
20 በመቶ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች አሰሪ መስሪያ ቤቶች የተሟላ መረጃ ባለማቅረባቸው የተነሳ የጡረታ መለያ ቁጥር እንዳልተሰጣቸው ተገልጿል።
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ እውነቱ ዘካሪያስ እንደገለጹት በሁለቱ ዞኖች ከ21 ሺ በላይ የመንግስት ሠራተኞች የሚገኙ ሲሆን የጡረታ መለያ ቁጥር ያላቸው ከ80 በመቶ አይበልጡም።
20 በመቶ የሚሆኑት አሰሪ መስሪያ ቤቶች የተሟላ መረጃ ባለማቅረባቸው የተነሳ የጡረታ መለያ ቁጥር እንደሌላቸው ነው ያነሱት።
ይህም ግለሰቦች በተለያዪ ምክንያቶች ጡረታ ለመውጣት አገልግሎት ፈልገው ወደ መስሪያ ቤቱ ሲመጡ ለእንግልትና አላስፈላጊ መመላለስ እየዳረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ መለያ ቁጥር ለመስጠት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሁለቱ ዞኖች በዓመት ከ250 በላይ ጡረተኞች የአበል ውሳኔ እንደሚያገኙ ያነሱት ኃላፊው አሰሪ መ/ቤቶች የሠራተኛውን መረጃ አደራጅቶ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
መረጃዎች ተደራጅተው ከቀረቡ የአንድ ማህደር የውሳኔ ስታንዳርድ ሁለት ሰዓት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመት ከሁለቱ ዞኖች 128 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የጡረታ መዋጮ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከ2015 በጀት ዓመት የዞረ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ውዝፍ ዕዳ ለማሰባሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
አሰሪ መሥሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮ ገቢ አዋጁ በሚደነግገው መሰረት ገቢ ከማድረግ ይልቅ በጀት ሲመጣ እንተካለን በሚል ከታለመለት ዓላማ ውጭ መጠቀም፣ አመራሩ የጡረታ መዋጮ በወቅቱ ገቢ እንዲሆን እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት አነስተኛ መሆን ችግሮች የተስተዋሉ ሲሆን ህጉና አዋጁ በሚደነግገው መሰረት ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አያይዘውም ለብሔራዊ መለያ ቁጥር የቅድመ ዝግጅት ሥራ በየደረጃው የሚገኙ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያዎች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የጽ/ቤቱ የደንበኞች አገልግሎት ምዝገባ ባለሙያ የሆኑት አቶ እሸቱ ጀማነህ በበኩላቸው በሁለቱ ዞኖች 2, ሺህ 234 ጡረተኞች የአበል ክፍያ እንደሚያገኙ ተናግረው ከ21ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች መረጃ በተቋሙ እንደተደራጀ ተናግረዋል።
በጽ/ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ገድለ ጊዮርጊስ ሀብታሙ የሁለቱ ዞኖች ተጧሪዎችና ለተቋሙ የተሟላ መረጃ የደረሰላቸው የመንግስት ሰራተኞች በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ መረጃቸው መደራጀቱን አብራርተዋል።
ካነጋገርናቸው ተጧሪዎች መካከል አቶ አሽኔ አመኑና ወይዘሮ ያቦነሽ አባቴ በሰጡት አስተያዬት አሰሪ መስሪያ ቤቶች በሚያሳዩት የመረጃ አያያዝ ችግር ለአገርና ለህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዜጎች በጡረታ መውጫ ዕድሜያቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ