ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ምርቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችሉ አርሶ አደሩ የደረሱ ምርቶችን በወቅቱ ሊሰበስብ እንደሚገባ ተጠቆመ

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ምርቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችሉ አርሶ አደሩ የደረሱ ምርቶችን በወቅቱ ሊሰበስብ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ምርቶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችሉ አርሶ አደሩ የደረሱ ምርቶችን በወቅቱ ሊሰበስብ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በሰብል ምርት ጥበቃ እና ድህረ ምርት አሰባሰብ ዙሪያ ለባለሙያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።

በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ ወራት በተለያዩ ሰብሎች በዘር  ከተሸፈኑት 378 ሺ 428 ሄክታር  ያህል ማሳ ላይ  7 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ  ክንፉ ገልፀዋል።

አቶ አሸናፊ  አክለውም በተለይም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የክልሉ ቆላማ እና ወይናደጋ  አከባቢዎች ላይ ምርቱ የደረሰ በመሆኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ  ምርቱን ሳያበላሽ በተገቢው መሰብሰብ እንዲያስችል እና ሰብሉን ከተለያዩ ተባዮች ለመከላከል ከሚዛን እጸዋት ጥበቃ ላብራቶሪ ጋር በመቀናጀት ከ6 ዞን እና ከ41 ወረዳዎች ለተወጣጡ የሰብል ልማት ባለሙያዎች  ግንዛቤ የማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ምርቱን ከመሰብሰብ አንጻርም አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በርብርብ ሊሰሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ምርቱ ባልደረሰባቸውም አከባቢዎች አርሶ አደሩ ተገቢውን የአረም ቁጥጥር ስረአቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የሚዛን እጸዋት ጥበቃ ክሊኒክ ሀላፊ አቶ እያሱ አስፋው በበኩላቸው ክሊኒኩ በተለይም በመስክ አሰሳ  እንዲሁም በተቋሙ ላብራቶሪ ልየታ  በሰብል ላይ የሚደርሱትን ጉዳቶች ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመኖሩ በምርት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ከአረም ቁጥጥር ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ባሉት ሂደቶች ላይ ለሰብል ልማት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠታቸውን ተናግረው ሰልጣኞችም ባገኙት ግንዛቤም ወደአከባቢያቸው ሲመለሱ ለባለሙያዎች እና ለአርሶአደሮቹ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ከሰልጣኞች መካከልም አቶ ብረሀኑ ግርማ ከካፋ ዞን አቶ አለማየሁ ዋዱ ከደውሮ ዞን እንዲሁም አቶ መከተ ያሬ ከኮንታ ዞን በበኩላቸው በተለይ በአርሶ አደሩ ከአረም ቁጥጥር ጀምሮ መዘናጋት መኖር ማሳውን በዘር ከሸፈነ በኋላ ቅኝት አሰሳ አለማድረግ ባለሙያዎች ክትትል አለማድረግ ጉድለቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

 አሁን ባገኙት ግንዛቤም ወደታች ወርደው ለአርሶ አደሩና ለባለሙያው በማስጨበጥ የሰብል ቁጥጥር ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ  – ከሚዛን ጣቢያችን