በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ዞናዊ ንቅናቄና የምክክር አካሔደ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ዞናዊ ንቅናቄና የምክክር አካሔደ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ዞናዊ ንቅናቄና የምክክር መድረክ በጂንካ ከተማ አካሂዷል፡፡

መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን  ገምግሟል፡፡

ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን በማጎልበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዞኑ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም በልዩ ሁኔታ መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ እንደገለፁት፥ ወጣቱ በኢኮኖሚ በማህበራዊ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አንስተው በብድር አመላለስ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በግብርና 4ሺ 467 በኢንዱስትሪ፣ 2ሺ 481 በአገልግሎት ዘርፍ፣ 2ሺ 978 በጠቅላላው  9ሺ 926 ለሚሆኑ ወጣቶች አዋጭ የቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክብራን ሰንሚ ገልፀዋል፡፡

ኃላፊው አክለው ዕቅዱን ለማሳካት የዞኑ ፀጋዎች በመለየት፣ የቁጠባ ሞብላይዘሽን ሥራ ላይ በማተኮር  17 ሚሊዬን 065 በማስቆጠብ፥ 29 ሚሊዬን 119 ሺ ብድር በማስመለስ 49 ሚሊዬን 561 ሺ 280ብር ገንዘብ በማሰራጨት የወጣቱ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሩብ ዓመቱ አፈፃፀም የተለዩ ማነቆዎችን በመፍታት በቀጣይ 90 ቀናት ዕቅድ ላይ በማካተት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መድረኩ ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን