ከሆልቴ ሠገን መንገድ የሠገን ዶዴ ድልድይ ለብልሽት በመዳረጉ መቸገራቸውን በጋርዱላ ዞን ካነጋገርናቸዉ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ተናገሩ

ከሆልቴ ሠገን መንገድ የሠገን ዶዴ ድልድይ ለብልሽት በመዳረጉ መቸገራቸውን በጋርዱላ ዞን ካነጋገርናቸዉ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ተናገሩ

ድልድዩ ተደርምሶ በሰዉና ንብረት ላይ አደጋ እንዳይፈጥር ተለዋጭ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ጊዜያዊ ድልድይ እንዲሠራ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የጋርዱላ ዞን መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ ድልድዩ ባለፈዉ በጀት ዓመት መሰንጠቁን ገልፆ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዞኑ ነዋሪዎች መካከል አስተያየት የሰጡት አቶ አብሮ ኩጮ ሆልቴ ሠገን የሚወስደዉ መንገድ ድልድይ በመበላሸቱ ምክንያት ተለዋጭ መንገድ ቢሠራም ጊዜያዊ ድልድይ ባለመኖሩና ኮረት በአግባቡ ባለመጨመሩ በዝናብ ወቅት ለአገልግሎት ምቹ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ከአሽከርካሪዎች መካከል አቶ ይርጋለም ማሞ እንደተናገሩት ከሆልቴ ሠገን መንገድ ሰፊዉን ህብረተሰብ የሚያገለግል ድልድይ በመሰንጠቁ የተሠራዉን ተለዋጭ መንገድ እየተጠቀሙ ቢቆዩም አሁን በክረምት ወቅት ተለዋጭ መንገዱም በደለልና በጎርፍ በመበላሸቱ መልሰዉ ድልድዩን ለመጠቀም መገደዳቸዉን ገልፀዋል፡፡

የጋርዱላ ዞን መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ ምክትል ሃላፊና የመንገድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደነበ ዳራ እንደገለፁት ድልድዩ ባለፈዉ በጀት ዓመት በመሰንጠቁ ለክልል ገጠር መንገድ አርባ ምንጭ ዲስትሪክት አሳዉቀዉ ተለዋጭ መንገድ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

ባለፈዉ ግንቦት 2015 በበጀት መዝጊያ ላይ የድልድዩ ብልሽት ታዉቆ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ቢያሳዉቁም በበጀት ማለቂያ ላይ በመሆኑ ሥራዉ በአግባቡ በበጀት አስደግፈዉ ለመሥራት ምቹ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተሠራዉ ተለዋጭ መንገዱ በደለልና በወንዝ ሙላት ለአገልግሎት ምቹ ባለመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ በ2016 ዓ.ም በበጀት አስደግፈዉ እንደሚሰራ ከስምምነት መድረሳቸዉን የገለፁት አቶ ደነበ ከክልል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ በወቅቱ ወደ ሥራ ባለመገባቱ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ካታንሾ ካርሶ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን