የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ምክር ቤት 18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ መቱ አኩ እንደተናገሩት፥ ምክር ቤቱ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በክልሉ ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በየአመቱ ህዳር 29ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ በሀገር አቀፉ ደረጃ በሶማሌ ክልል እንደሚከበር ጠቁመዋል።
18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የበለጠ ያማረና የተሳካ ለማድረግ በክልሉ ለማክበር የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ በአሉን ለማክበር ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፥ በክልሉ ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።
በተለይ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ነባር እሴቶቻቸውን የሚለዋወጡበት፣ ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ሁነት እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።
በዓሉ “ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል ያሉት አቶ መቱ፥ በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች በሚገኙ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የትምህርት ተቋማቶች፣ የመንግስት ሰራተኛውና እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ የፓናል ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር መስፍን ወዳጆ በበኩላቸው፥ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ በአሉን ባመረና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ለማቅረብ የሚዲያ አካላትም ከወዲሁ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
እንደ ክልል በአሉ ሲከበር የመገናኛ ብዙሃን የህገመንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮዎችን ትኩረት በማድረግ መረጃዎችን ለአድማጭ ተመልካቹ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በመድረኩ ላይ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦንጋ የማሻና የሚዛን ኤፍ ኤም ቅርንጫፍ ጣቢያ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በሁሉም የብሔረሰብ የስርጭት ቋንቋዎች በዓሉን የሚዘክሩ ዜናና ፕሮግራሞች በማዘጋጀት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በዘንድሮው አመት ህዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ