በ2016 1ኛ ሩብ ዓመት ላይ 1መቶ 42ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2016 1ኛ ሩብ ዓመት ላይ 1መቶ 42ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በያዝነው በጀት ዓመት ጽህፈት ቤቱ ከመደበኛ 5መቶ 16 ሚሊዮን 7 መቶ 5ሺህ 5 መቶ 52 እና ከማዘጋጃ ቤት 90ሚሊዮን 5መቶ 91ሺህ 4መቶ 57 በድምሩ 6መቶ 7ሚሊዮን 2መቶ 97 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ታደሰ እንደገለፁት፤ በ2016 መጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ 1መቶ 42ሚሊዮን 1መቶ 96ሺህ 4መቶ 65 ገቢ ተሰብስቧል።

የዘንድሮው በጀት ከአምናው አንፃር ከመቶ እጅ በላይ የበለጠ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በሩብ ዓመት የተሰበሰበው ገቢ ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 60 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።

የደረጃ ሐ የገቢ ትመና፣ 73 የደረጃ ሽግሽግ የተደረገላቸው ግብር ከፋዮች እና ሌሎችም የተሠሩ ሥራዎች የገቢ አቅም እንዲጨምር የራሱን አሰተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው በተለይም ደረጃ ለ እና ሀ ግብር ከፋዮች አካባቢ ደረሰኝ መሰጠት ላይ ጉድለት መኖሩን ለአብነት አንስተዋል።

ከደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች አሥራ አንድ ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ያሉት ኃላፊው የግብር መክፈያ ጊዜ እስከ ጥቅምት 30 ብቻ ሰለሆነ በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የገቢ ቋቶችን ሁሉ አሟጠው በመሰብሰብ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ እንዲቻል የፍትሕ አካላትና ባለድርሻዎች የጋራ ቅንጅት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

በከተማው ደረሰኝ የማይሰጡ ነጋዴዎች ላይ በየቀኑ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ መብራቱ ህብረተሰቡም ግብይት ሲፈጽም ደረሰኝ በመሰውድ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።

በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ የከፈሉ ግብር ከፋዮችን ያመሰገኑት ኃላፊው ለሕግ ተገዢ ያልሆኑ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቁመው ህግ የማስከበሩንና የገቢ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ገበና – ከፍስሃ ገነት ጣቢያችን