በዞኑ መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት ይሠራል – የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችንም ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
ይህ የተገለጸው በከተማው በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ ከፈታ ሥራዎችን የዞንና የከተማ አመራሮች የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት ነው።
የጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አረጋ በደቻ እንደገለጹት በዞኑ ባሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መሠረተ ልማት የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው።
በዞኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር በተለያዩ ቦታዎች ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ከፈታ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ አረጋ ህብረተሰቡ በመንገድ መሠረተ ልማት ያሳየውን አንድነትና ተነሳሽነት በሌሎች የልማት ዘርፎችም እንዲደግም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ህብረተሰቡ የተለያዩ ሰብሎችን ያለምንም ክፍያ በማንሳት ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረውን አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ብር በላይ በሌላ ልማት እንዲውል ማድረጉን ገልጸዋል።
በከተማው በተያያዘነው ዓመት የመንገድ ከፈታ፣ የከተማ አስተዳደር ህንፃ ግንባታ፣ 22 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ሥራ እና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠራ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሺፈራው ተናግረዋል።
በዚህም ህብረተሰቡን በማስተባበር ወደ 38 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ከፈታ ለማከናወን ታቅዶ እስከ አሁን 20 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ መከናወኑን ከንቲባው አስረድተው የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ልማትን ለመንግሥት ብቻ መተው ተገቢ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ዳንኤል ከተማ አስተዳደሩ እያካሄደ የሚገኘውን የልማት ሥራ ሊያደናቅፉ የሚሹ አካላት ከእኩይ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሌሎች በመሰክ ምልከታው የተገኙ አካላትም ህብረተሰቡ በመንገድ ልማት ዘርፍ እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከፍስሃገነት ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ