አደምስ ቴርማል ፋውንዴሽን የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጀት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለአካል ጉዳተኞች የዊሊቼር ድጋፍ አደረገ

አደምስ ቴርማል ፋውንዴሽን የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጀት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለአካል ጉዳተኞች የዊሊቼር ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) አደምስ ቴርማል ፋውንዴሽን የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጀት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በሀዲያ ዞን ለሚገኙ 2 መቶ 26 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የዊሊቼር ድጋፍ አድርጓል።

የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤትና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች እንዲንቀሳቀሱ ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል።

”አዳምስ ቴርማል ፋውንዴሽን” የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ከ10 ዓመት በፊት በሀዲያ ዞን በይፋ ስራውን ጀምሮ በትምህርት፣ በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በአካል ጉዳተኞችና ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን መረዳት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።

ፋውንዴሽኑ በሰሜን አሜሪካ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት መጋቢ ሳሙኤል ጌታቸው ድርጅቱ በሀዲያ ዞን በሆሳዕና እና በዱና ወረዳ ኦቶሮ አከባቢዎች ከዓመታት በፊት ስራ በመጀመር ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 3 መቶ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ የሚገኝ አጋር ተቋም ነው ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ”ሴንትራል ቸርች እና” ሆፕ ኦፍ ሄቨን” የተሰኙ አጋር ተቋማትን በማስተባበር በጠቅላላው ከ10ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ2 መቶ 26 አካል ጉዳተኞች የዊሊቸር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ወስጥ 20 ዊሊቸሮች ለንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማበርከቱን አመላክተዋል ።

የአደምስ ቴርማል ፋውንዴሽን የሀገር ወስጥ ተወካይ የሆኑት አቶ ነጋ መገርሳ በበኩላቸው ድርጅቱ ኢትዮጵያ ወስጥ በህፃናትና በእናቶች ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልፀው በተለይም አካል ጉዳተኞች የመማር ዕድልና አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት የሚሆኑ ችገሮችን መቅረፍ ላይ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ድርጅቱ በዋናናት ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን በአከባቢው የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ የዳሰሰ ጥናት በማድረግና ፕሮጀክት በመቅረጽ በትምህርት ወቅት ማቋረጥ ለሚያጋጥማቸው ተማሪዎች ችግሮችን የመለየት ስራ መከናወኑን የተናገሩት ደግሞ የሆሳዕና ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር ዣቪ በቀለ ናቸው።

ከሰሜን አሜሪካ ከሴንትራል ቸርች እና ከሆፕ ኦፍ ሄቨን የተገኙ አጋር አካላትም በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመት ለተለያዩ ችግር የተዳረጉ ወገኖች በማገዝ ረገድ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰው የአካል ጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ሲደሰቱ በማየታቸው መደሰታቸውን  ጠቁመዋል።

በድጋፍ ርክብክቡ የተገኙት የሀዲያ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሴ አዋቶ እንዳሉት፤ በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች አካል ጉዳተኞችን የመመልመል ስራ ሲከናውን መቆየቱን አስታውሰው ለተደረገው ድጋፍ ለአጋር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ሔኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን