የቡርጂ ዞን አርሶ አደሮች ለመኸር እርሻ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን ገለጹ

የቡርጂ ዞን አርሶ አደሮች ለመኸር እርሻ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን ገለጹ

ሀዋሳ፡ መስከረም 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡርጂ ዞን አርሶ አደሮች ለመኸር እርሻ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የመኸር እርሻ 85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች እንደሚሸፈን ይጠበቃል።

በዞኑ አርሶ አደር ማሞ ጦዴ እና ታከለ ዴኮ ወቅቱ የሰጠውን ዝናብ ተጠቅመው ለመኸር እርሻቸው ማሳቸውን እያዘጋጁ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በአከባቢው ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት በችግር እንዳሳለፉ ያስታወሱት አርሶ አደሮቹ፥ የመኸር ወቅት የዝናብ ስርጭት ጥሩ በመሆኑ ወደ ምርታማነት ተመልሰናል ብለዋል።

በዞኑ የኦቶሞሎ ቀበሌ ግብርና ባለሙያ የሆኑት አሚና ሹና በቀበሌው ያሉ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ለመኸር እርሻ በጊዜ ማዘጋጀት እንደጀመሩ እና በብዛት ቡራ ቡርጂ ቦሎቄ እና ጤፍ እንደተዘራ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ባለፉት ዓመታት በአከባቢው ተከስቶ በነበረው ድርቅ በመማር በመኸር እርሻ ምርታማ እንዲሆን ጠንክረን እየደገፍናቸው ነው ያሉን ደግሞ በዞኑ የቲሾ ቀበሌ ግብርና ባለሙያ አቶ ታሪኩ ሙሉ ናቸው።

የቡርጂ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ህርቦ በጦ በዘንድሮው የመኸር እርሻ 85 ሺህ 696 ሄክታር ማሳ ተዘጋጅቶ በዋና ዋና ሰብሎች በቡራ ቡርጂ የቦሎቄ እና በጤፍ መሸፈኑን ገልፀዋል።

በግብዓት በኩል 4 ሺህ 760 ኩንታል NPS እና 510 ኩንታል ዩሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ያብራሩት ኃላፊው፥ የዝናቡ ስርጭት በዚህ ከቀጠለ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከፍስሃገነት ጣቢያችን