ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በመስጠት አህጉራዊ መርህን በተግባር ማሳየት መቻሉን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ
ሀዋሳ፡ መስከረም 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በመስጠት አህጉራዊ መርህ በተግባር ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፥ ስምምነቶች ወደ ተግባር ተቀይረው በመልሶ ግንባታ መዕራፍ ላይ ነን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት በንግግር መፍታት መቻላችን ለብዙዎች እፎይታን የፈጠረ ከመሆኑም በላይ፥ ጠመንጃና ኃይል ልዩነቶችን የመፍታት አማራጭ ማክተም እንዳለበት በተግባር ያሳየንበት ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ከማንኛው ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት አለው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ምንጊዜም ቢሆን ለንግግርና ለሰላም የሚረፍድ ጊዜ የለም ነው ያሉት፡፡ ተነጋግረን ባንግባባ እንኳ ጦርነት አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡
ጦርነት አንድ አሸናፊ ብቻ ይፈጥራል ያሉት ርዕሰ ብሔሯ፥ ውይይት ግን ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፤ አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁላችንም መሆኑን በመረዳት በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን በማቆም የሠላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጭ የተሻለ አማራጭ የለም ነው ያሉት፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያደሩና የነበሩ የሃሳብ ልዩነቶችን ለማስታረቅና ለማቀራረብ ብሎም ወደ ተሻለ መግባባት እንደሚወስድ ገልጸው፥ የቀደመ ዝንፈቶችና ክፍተቶችን በማረም የወደፊት እድላችንን ተመካክረን በማቅናት የተሻለች ኢትዮጵን የመፍጠሩ እድል በእጃን ነው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ያጣነውን ለማረም፣ የያልተገግባባነውን ለማግባባት፣ የተሠበረውን ለመጠገን፣ የተጣመመውን ለማቅናት፣ የተራራቀውን ለማቀራረብ፣ ዳርና ዳር ያለውን ወደ መሐል ለማምጣት ለሁላችንም የምትሆን ሐገር ለመገንባት፣ ሁላችንም ተግባብተንና ተማምነን መሰረት የምንጥልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በተያዘው በጀት አመት ወደ ምክክር ምዕራፍ ይሸጋግራል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ልዩነታችንን በማጥበብ፣ አብሮነታችንን አጉልተን በሀገረ መንገስት ግንባታ ሂደት የታዩ መሠረታዊ ስብራቶችን አክመን የተረጋጋ ሀገረ መንግስት መፍጠር ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከሀገራዊ የምክክር መድረኩ ምንም መጉደል የለበትም ያሉት ፕሪዚዳንቷ፥ ድርሻ ያለው ሁሉ እንዲሳተፍ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ