የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶች ማህበር ሁለተኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ዘይኑ ሻውዲን እንደገለጹት የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶች ማህበር (ኢወማ) ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በአረንጓዴ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች በመሳተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል ::
ሰላምን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
በቀጣይም ውስጣዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት የበለጠ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የቀቤና ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ እጩ ዶ/ር ሀቢብ ከድር ማህበሩ በኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ኤጀንሲ ህጋዊ እውቅና ካገኘበት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልፀዋል።
የብሔረሰቡ የዘመናት ጥያቄ የነበረው በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ህጋዊ መስመርን ተከትሎ በመታገል ለውጤታማነቱ በሀገር ውስጥና በወጪ ሀገራት የሚኖሩ የማህበሩ አባላት ሚና የጎላ እንደነበር አስረድተዋል::
የቀቤና ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ሀያቱ ሁሴን በበኩላቸው ማህበሩ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ያሉ አባላቱን በማደራጀትና ዋና መቀመጫውን ወልቂጤ ከተማ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝና አሁን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 10 ቅርንጫፎች እንዳሉት ተናግረዋል::
የመድረኩ ተሳታፊ የማህበሩ አባላት በሰጡት አስተያየት በቀጣይ ማህበሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ::
ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የማህበሩ አባላትና አመራሮች : የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ወጣቶች የተገኙ ሲሆን በማህበሩ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አባላትና አመራሮች የእውቅናና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ::
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ- ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ