የጎፋ ዞን የሣውላ ከተማ በህዝብ ተሳትፎ ለሚገነባው የባናካ ተራራ መዝናኛ ፓርክ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የከተማው ነጋዴዎች ተናገሩ

አካታች የልማት ፕሮጀክት ግንባታው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚገነባ የሚታወስ ነው።

በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ባናካ ተራራ ላይ በህብሰተሰቡ ተሳትፎ የመዝናኛ ፓርክ ለመገንባት ከሳምንታት በፊት ወደ ስራ ተገብቷል።

ስራው ባለበት ደረጃና ቀጣይ ድጋፍ ዙሪያ ከከተማው የንግድ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ተሳታፊዎቹ አንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር የቱሪስት መዳረሻና ወጣቶች ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያና መዝናኛነት ምቹ ቦታ በመሆኑ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ እሸቱ ስራው ከ1 መቶ 11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ መሆኑንና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሰለሚጠናቀቅ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አስፈልጓል ብለዋል።

የሣውላ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ጳውሎስ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚገነባውን ይህንን ሰፊ የፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ የመንገድ ከፈታን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

የሳውላ ከተማ የመንግስት ዋና ተጠሪ ኃላፊ አቶ አብርሃም ብርሃኑ የባናካ የፕሮጀክቱ ግንባታ በሣውላ ከተማ የቱሪስት መዳረሻና የመዝናኛ ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ከንግዱ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያስነሳውን የሶዶ-ሳውላ የመንገድ ግንባታ ኘሮጀክት መጓተት ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው አካል ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ: ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን