በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በኦሮሚያ ክልል መንግስት ድጋፍ 80 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባዉ የጉስባጃይ ኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
ሀዋሳ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በኦሮሚያ ክልል መንግስት ድጋፍ 80 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባዉ የጉስባጃይ ኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
ይህ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ የተገነባው ትምህርት ቤት የትምህርት ሽፋንና ጥራት ከማረጋገጥ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ እንዳሉት በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ የተገነባው የጉስባጃይ ኢፋ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ደረጃ ትምህርት ቤት መመረቅ የትምህርት ፍትሀዊነትንና ጥራትን ከማረጋገጥም ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው፡፡
በተናጥል ብቻ በማልማት ሊረጋገጥ የሚችል እድገት የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁለቱም ህዝቦች በሁሉም መስክ አብሮ እየሰሩ ያሉትን ስራ አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵየ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ህዝቦች በጋራ እንዲሰሩ እንዲያለሙና እንዲለወጡ ማድረግ የመንግስት ተግባር እንደሆ ገልፀዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ እንዲሁም አመራሩ በጉራጌ ዞን ኢኖር ወረዳ ይህን የመሰለ ግዙፍ ፕሮጀክት ገንብተው ስላበረከቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብና መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት በቀለ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለውን በጎ መስተጋብር ለማጠናከር ከትርፉ ሳይሆን ከጎደለው በመቀነስ በአምስት ክልሎች ኢፋቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል በማድረግ ላይ ሲሆን ከእነዚህም ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ የጉስባጃይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ስምንት ብሎኮች ያሉት ሲሆን ባለሁለት ወለል 18 የመማሪያ ክፍሎችና ልዩ ልዩ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ ቤተ-ሙከራ፣ ቤ-መፅሀፍት፣ የስልጠና መስጫ ክፍሎችንና ሌሎችንም አሟልቶ መያዙን ገልፀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተገነባው ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥም ባለፈ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ይቀርፋል ያሉት ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ይታገሱ አርጋውና መኑር አወል ናቸው፡፡
ዘጋቢ፡ ብርሀኑ ማሞ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ