ሕጋዊ የንግድ ሂደትን ተከትለው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የጎፋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሕጋዊ የንግድ ሂደትን ተከትለው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የጎፋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ገልጿል።
መምሪያው ያለፈውን አመት ማጠቃለያና በ2016 ዕቅድ ስምሪትና በሩብ አመቱ አፈጻጸም ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ግምገማ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ትዝታ አብረሃም የንግድ ስራን ለማዘመን የቀጥታ ኢንተርኔት ትስስር አገልግሎት ለመጀመር ታቅዶ በ7 መዋቅሮች ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
ከኤክስፖርት ምርት አቅርቦት አኳያ ማሾ፣ ሰሊጥና ቀይ ቦለቄን ጨምሮ 5ሺህ 33 ቶን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
ለንግድ ስረዓቱ ፈተና የሆነውን ህገ-ወጥ ንግድ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ህገ-ወጥ ደላላዎችና በደረሰኝ ግብይት አለመፈጸም የመሳሰሉ ችግሮችን ለማረም እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም በቀጣይም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጎፋ ዞን የንግድ ስርዓትን የማዘመንና ገበያን የማረጋጋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ የንግዱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
ገበያን በማልማት፣ አምራችና ሸማችን በማገናኘት የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማስተካከል ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ማህበራትንና ኢንተርፕራይዞችን በማበረታታት፣ የንግድ ስርዓት በማዘመን በሂደት ገበያው ራሱን በራሱ እያስተዳደረ እንዲሄድና እንዲጠናከር አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ልማት ዕቅድና በጀት ግምገማ ተወካይ አቶ ፍሬው በቀለ ያለፈውን አመት እቅድ ክንውን፣ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ስምሪትና በሩብ አመቱ አፈጻጸም ዙሪያ የተዘጋጀውን ሪፖርት አቅርበው በተሳታፊዎች ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የተሻለ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ በተሳታፊዎች ተነስቷል።
የንግድ ፍቃድ እድሳትና ስረዛ፣ በደረሰኝ ግብይት መፈጸም፣ የሰንበት ገበያዎችና የሕገ-ወጥ ደላላዎች ቁጥጥር ዙሪያ የታዩ ክፍተቶች ተገምግመዋል።
ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በሚያመርቱና ለማዕከላዊ ገበያ በሚያቀርቡ አካባቢዎች የሚስተዋለው ህግን ለመጣስ የሚሞክር የገበያ ሰንሰለት በፍጥነት መታረም እንደሚገባው በተሳታፊዎች አስተያየት ተካቷል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ