የብሔረሰቦች ቀን በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ተገለጸ

የብሔረሰቦች ቀን በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የብሔረሰቦች ቀን በዓል ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ተገልጿል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የ18ኛው ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ቀን በዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ በመሪ ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ የብሔረሰቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ገልፀዋል።

ዋና አፈ ጉባኤው አክለውም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሶማሌ ክልል ጂጂጋ ከተማ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቀን በዓል ብዝሃነትን በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ በበኩላቸው የብሔረሰቦች ቀን በዓል በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦች እንዲነትን ከማጠናከር ባለፈ የክልሉን የተለያዩ የባህል እሴቶችን ለሌላው ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሆነም አንስተዋል።

በመድረኩ የበዓሉ መሪ ዕቅድ በፌደራል ደረጃ ፀድቆ የመጣ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በክልል ደረጃ ተገምግሞ ከፀደቀ በኃላ በዞንና በወረዳዎች በተመሳሳይ ውይይት ተደርጎና ፀድቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ተብራርቷል።

በመድረኩ የክልሉ የበዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን