በሆሳዕና ከተማ ህብረተሰቡ በመንገድ ግንባታ ሂደት የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሆሳዕና ከተማ እየተገነባ በሚገኘው የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሂደት በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል፡፡
የከተማው የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካሪ ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳዳር ከንቲባና የፕሮጀክቱ ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሊሬ ጀማል እንደገለፁት በከተማው በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 60 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው።
የዚሁ አካል የሆነውና በከተማው እየተገነባ የሚገኘው የ20 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ሥራ የደረሰበት ደረጃ ያሉንን አቅሞች በማስተባበር ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት ከንቲባው በትግበራው ሂደት በህዝቡ ዘንድ የታየው መነቃቃትና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የፕሮጀክቱ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም መጫ በሆሳዕና ከተማ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው ከነዚህም መካከል ከተማዋን የሚመጥን መንገድ ካለመኖሩ የተነሳ በቁጭት የተጀመሩና እየተገባደዱ ያሉ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በፕሮጀክቶቹ ትግበራ ሂደት ያለምንም ካሳ ክፍያ ቤት ንብረቱን በማንሳትና ድጋፎችን በማድረግ ነዋሪው እያደረገ ያለው ተሳትፎና የከተማው አመራርና ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት የሚበረታታና ለሌሎች ከተሞችም መነቃቃትን የሚፈጥር እንደሆነ አንስተዋል።
በ2014 በጀት ዓመት የተጀመረው 14 ነጥብ 134 ኪሎ ሜትር የሆሳዕና ከተማ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ፊዚካል አፈፃፀሙ 70 ከመቶ እና ፋይናንሻሉ 40 ከመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ኃይሌ ለጠቅላላ ጉባኤው ካቀረቡት ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል።
በእስከ አሁኑ ሂደት ከ3 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት መንገድ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት በታየው በጣለው ከፍተኛ ዝናብና በተለያዩ ምክንያቶች ስራው በተያዘለት ጊዜ ካለመጠናቀቁ የተነሳ ከአማካሪ ድርጅቱ በኩል በተጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ የ214 ቀናት ውል ተገብቶ ቀሪው ግንባታ እስከ መጪው የካቲት ወር እንዲጠናቀቅ ከስምምነት ስለመደረሱም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በ495 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታ የተጀመረው የ5 ነጥብ 65 የነባሩ አስፋልት መንገድ ደረጃ የማሻሻል ፕሮጀክት ሥራ በ18 ወራት ለማጠናቀቅ አየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በመድረኩ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ኦዲት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ከቦርድ አባልነት በለቀቁ አባላት ምትክ ምርጫ ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል- ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ