ሁሉም ማህበረሰብ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ በመጠበቅና በመንከባከብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት አሳሰበ
ሀዋሳ፡ መስከረም 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሁሉም ማህበረሰብ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ በመጠበቅና በመንከባከብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት አሳስቧል።
በዞኑ በሁለተኛ ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
የጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ እንዳሉት፤ ጌዴኦ በመልክዓ ምድር አያያዝ የሚታወቅ ማህበረሰብ በመሆኑ ባህላዊ፣ ሰው ሰራሽ ጥብቅ ደኖችና የጥምር እርሻ ባለቤት ስለሆነ አሩንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዚሁ ልክ በትኩረት ተሰርቷል።
በገጠር ቡና፣ እንሰት፣ ሀገር በቀል ዛፎችና የተለያዩ ፍራፍሬዎች እንዲሁም በከተማ ለውበት የሚሆኑ የጥላ ዛፎች መተከላቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የመሬት ለምነትነን ለመጠበቅ፣ አፈሩ በጎርፍ እንዳይሸረሸር ለመከላከልና የተፈጥሮን ሥነ-ምህዳር በማስተካከል ረገድም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች እንደላቸው ተናግረዋል።
ለካርቦን ልህቀት የማይበገር አረንጋዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ የአረንጓዴ አሻራ የማይተካ ድርሻ አለው ያሉት አቶ ዮሐንስ የአሁኑ ትውልድ የተተከሉ ችግኞችን ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመጠበቅና በመንከባከብ ለነገ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ማህበራዊ ኃላፊነትን በአደራ ጭምር እንዲወጣ አሳሰበዋል።
የ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ-መርሃ ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፌደራልና የቀደመው የደቡብ ክልል አመራሮች መጥተው አሻራቸውን ያሳረፉበት በመሆኑ ለየት ያደረገዋል ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ።
የጌዴኦ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት የደን ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ዕድሉ አወቀ 2015 ዓ.ም በሁለተኛ ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ 3.5ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 3.9ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል።
ይህ ከዕቅድ በላይ እንዲሳካ የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ያበረከቱት አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ተናግረው ይህን መልካም ዕሴት ጠብቀውና ተንከባክበው ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል ከግንዛቤ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አቶ ዕድሉ ገልጸዋል።
በቀጣይ የጽድቀት መጠኑን ለማረጋገጥ ቆጠራ በማድረግ የድጋፍና ክትትል ሥራ እንደሚያጠናክሩም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከፍስሃ ገነት ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ