በአከባቢው ዘላቂ ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ መስከረም 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአከባቢው ዘላቂ ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ከጂንካ ከተማ ከተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የከተማውና የአሪ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በ2014 ዓ.ም ከአሪ ዞን ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ የተሳሳተ አካሄዶች አለመግባባትና ግጭት ተፈጥሮ በርካታ ቁሳዊና ማህበራዊ ጉዳቶች ደርሰዋል።
በዚህም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አካላትን ወደ ቦታቸው መመለስ እና በአሪና በሌሎች የአከባቢው ነዋሪዎች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎችን በእርቀ ሠላም ለመፍታት ያለመ መድረክ ተዘጋጅቶ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ከውይይቱ ተሣታፊ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ መኳንንት ደጀኔ፣ አቶ ትዳሩ አሰፋ፣ አብዱልመልክ እብረሐይምና ሌሎች በጋራ እንደገለፁት በአሪ ዞን ምስረታ ማግስት ከሁሉም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለሠላም ቅድሚያ መሰጠቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረው ለዘላቂነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በቀጣይ ሠላሙ ዘላቂነት እንዲኖረው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ከ2 ዓመት በላይ ያስቆጠሩትን ወደ ቤታቸው ለመመለስና በጉዳቱ ምክንያት ያለጥፋታቸው የታሰሩት ፍትህ እንዲያገኙ መሰራት እንዳለበት አሳስበው በዚህም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
መድረኩን የመሩት የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስፋው ዶሪና የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ለተሣታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ቀናት መሰል መድረኮችን ችግሩ በዋናነት በተፈጠረባቸው የደቡብ አሪ ወረዳ አከባቢዎች ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱን አረጋግጠዋል።
በተፈጠሩ መድረኮችም ተመሣሣይ ሀሣቦች መነሳታቸውንና የመጨረሻውን ዕርቀ ሠላም ለመፍጠር ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንዳለ አመላክተው ማህበረሰቡ ባነሳው ሃሳብ ልክ ከመንግስትና ከኮሚቴው ጎን በመቆም ለሚጠየቁ ጉዳዮች ሁሉ ፍቃደኝነቱን በተግባር መሳየት አለባበት ብለዋል።
አሁን ላይ በአዲሷ አሪ ዞን የህግ የላይነትን ማስከበር፣ በግጭቱ ለተፈናቀሉት በአስቸኳይ ቤቶቻቸውን በመገንባት ወደ ቦታቸው መመለስና በጉዳዩ የታሰሩት ፍትህ እንዲያገኙ መስራት ቁልፍ ተግባር መሆኑን አመላክተው ከሁሉም በላይ ህብረተሰቡ ከጥላቻና ቂም ተላቆ ለልማትና ለሠላም ዝግጁ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ