የማንነት መገለጫዎችን የማሳደግና የመንከባከብ ሂደቱ ኢትዮጵያዊ የወል ማንነትን በሚያጠናክርና በሚያጸና መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲራመድ ማድረግ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ መሠረት ነው – ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ

ሀዋሳ፡ መስከረም 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማንነት መገለጫዎችን የማሳደግና የመንከባከብ ሂደቱ ኢትዮጵያዊ የወል ማንነትን በሚያጠናክርና በሚያጸና መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲራመድ ማድረግ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ መሠረት መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ተናገሩ::

የየም ብሔር የዘመን መለወጫ (ሄቦ) በዓልና የዞን ምስረታ ፌስቲቫል በየም ዞን ሳጃ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በታላቅ ድምቀት ተከብሯል::

ሄቦ በየም ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክብረ በዐል ሲሆን የሩቅና የቅርብ ቤተዘመድ የሚሰባሰብበት አንድነትና አብሮነት የሚጎላበት እንዲሁም በታላቅ ዝግጅት ደምቆ የሚከበር በዓል ነዉ።

የብሔረሰቡ ሄቦ በዓልና የዞን ምስረታ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ የማንነት መገለጫዎችን የማሳደግና የመንከባከብ ሂደቱ ኢትዮጵያዊ የወል ማንነትን በሚያጠናክርና በሚያጸና መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲራመድ ማድረግ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ መሠረት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃነት አምባ በመሆኗ ብዝሃነትን ውበት እና ምንዳ በማድረግ፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ዘላቂነት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በጋራ አረዳትና ቁርጠኝነት በመያዝ የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።

የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ሄቦ በዓልን ስናከብር እሴቶቻችንንና የብሔረሰባችን መገለጫ የሆኑ ልመናን መጸየፍ፣ ታማኝነት እና ጠንካራ የስራ ባህል የመሳሰሉትን በማጎልበትና በሚገባ በማልማት ለሕዝብ ተጠቃሚነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የዞኑ ምስረታም በይፋ ተበስሯል::

የዞኑን ልማት ለማስቀጠል የሚያስችል የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብርም ተካሂዷል::

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል::

ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን