አንድ እሽግ ደብተር ለአንድ ልጅ በሚል የተጀመረው በጎ አድራጎት ከ5 መቶ 20 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዳዉሮ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ
በበጎ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ወጣቶችን ተቋማዊ አደረጃጀት ኖሯቸው እንዲታገዙ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚሠራም የዞኑ ዋና አስተዳደር ገልጿል።
ወጣት በኃይሉ ማቴዎስ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የማኅበራዊ ትስስር ገጽን ተጠቅሞ ባሰባሰበው ገንዘብ በርካታ የበጎ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከተግባራቱም መካከል የታመሙትን ማሳከም፣ የአረጋውያን ቤት መሥራትና በየዓመቱ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት መማር ያልቻሉትን መደገፍ መቻል የሚጠቀሱ ናቸው።
በዘንድሮም የትምሀርት ዘመን በፌስ ቡክ ባደረገው ቅስቀሳ ለ5 መቶ 20 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማግኘት ተችሏል።
በድጋፍ አቅርቦት የተገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ታዬ እንደገለፁት ባለፈው የትምህርት ዘመን ለ3 መቶ 20 ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በዘንድሮም፣ በወጣት በኃይሉ ማቴዎስ አንድ እሽግ ለአንድ ልጅ በተደረገው ቅስቀሳ ለ5 መቶ 20 ተማሪዎች ድጋፍ ይደረጋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደምሴ በበኩላቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ለበጎ አላማ በማዋል ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚተጉ ወጣቶችን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሮ እንዲታገዙ ይሠራልም ብለዋል።
በዕለቱ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ በሰጡት አስተያየት የወጣት በኃይሉ ማቴዎስ አምና የጀመረውን በጎ ተግባር ያዩት ወጣቶች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክልሉ በርካታ ወረዳዎች የመተጋገዝ እና የመረዳዳት ባህል በማዳበር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ወጣት በኃይሉ ማቴዎስ በዕለቱ ለተገኙት እንግዶች እንዳብራራው በተለያዩ የሥራ መስኮች ወደተለያዩ ወረዳዎች በሚዘዋወርበት ወቅት በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን በመመልከት ተግባሩን ጀምሯል።
ከትምህርት ቁሳቁስ በተጨማሪ የአረጋውያን ቤት መሥራት፣ የታመሙትን ማሳከምና መሠል ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጿል።
በቀጣይም ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ይገኛልም።
በድጋፉ የተገኙት ተጋባዥ እንግዶች፣ አድናቂዎቹ እና ተማሪዎች ሰው ለሰው የሚደረገው እገዛ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ