ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ለደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አሰተላለፉ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት መልዕክት በበዓሉ ወቅት ተቸገሩትን በመርዳት ልናከብር ይገባል ብለዋል።
ለዘመናት ተቀብሮ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተጫነው ተራራ ከተደበቀበት ስውር ስፍራ ይወጣ ዘንድ በደመራ ሰማያዊ ምልክት የታየበትን ቀን ለምናከብርበት በዓል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ስገልጽ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ከተለየ አክብሮት እና ፍቅር መልዕክት ጋር ነው፡፡
የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ አስተምህሮቱ እና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም ባሻገር የሚያስተምረ እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ሤራ ብትሸፈንም በዘላቂነት ግን ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
ዛሬ ከምንም ነገር በላይ ለእውነት የምንቆምበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በዙሪያችን ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ስም ማጥፋቶች፣ የሐሰት ወሬዎች፣ አሳሳች አሉባልታዎች እና በስሜት የሚነዱ ማስመሰሎች እንዲሁም ከፋፋይ አስተሳሰቦች ተበራክተውብናል፡፡
እኛ በዓላማ ከጸናን፣ ካልተከፋፈልን ለሐሰተኞች ጆሮና ልቦናችንን ከነፈግን እውነት ብትቀበር እንኳን እንደ ታላቁ መስቀል ሁሉ ቢዘገይም ነጻ እናወጣታለን። የመስቀል በዓል የእንጨቶች ድመራ ነው፡፡ እያንዳንዱ እንጨት ተደምሮ ችቦ ይሠራል፡፡ እያንዳንዱ እንጨት ባንድ ሆኖ ታላቁን ደመራ ይፈጥራል፣ የራሱንም ድርሻ ይወጣል፡፡
ሀገራችን የደመራ ምሳሌ፣ ሁላችንም አንድ ላይ ተደምረን የምንቆምላትና የምንቆምባት፣ ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ የምንሰለፍባት ናት። ኢትዮጵያውያን የሚያገጥሙ ችግሮችን እንደ ደመራው ሁሉ አንድ ሆነን ተደምረን በጽናት በማለፍ ከፊታችን የሚጠብቀንን የተስፋ ቀን በጉጉት ልንጠባበቅ ይገባናል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በድጋሚ መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ፡፡

More Stories
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው ሁሉን አቀፍ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ መሆኑ ተገለጸ
የመድሀኒት ተቋማት ስታንዳርድ ትግበራ የዳሰሳ ጥናት ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሀግብር ተካሄደ
በዶሮ እርባታ ዘርፍ በመሰማራት የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን የየም ዞን ሣጃ ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ተናገሩ