ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሙሉ መልዕክቱም የሚከተለው ነው፡፡
እንኳን ለየነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
መውሊደል ነቢ በሚከበርበት እለት፣ ሙስሊሞች መስጂድ ሄደው፣ በጋራ፣ ጸሎት ያድርጋሉ፡፡ የታላቁን ነቢይ ስራዎች፣ አስተምህሮቶች ይዘክራሉ፡፡ ነቢዩ በህይወት ሳሉ የነበራቸውን፣ ትህትና፣ ደግነት፣ ይቅር ባይነት ያስታውሳሉ፡፡ ከመስጂድ ከወጡም በኋላ፣ ያላቸውን ከሌላቸው ጋር በመካፈል፣ ለወገኖቻቸው ሁሉ ትሁት በመሆን፣ የበደላቸውን ይቅር በማለት፣ እንደ ዲናቸው መሪ፣ ትህትናን፣ ደግነትን እና ይቅር ባይነትን በተግባር ይፈጽማሉ፡፡
የየትኛውም እምነት ተከታዮች የሆንን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ በዚህ ታላቅ በዓል ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር አንድ ሆነን፣ ትህትናን፣ ደግነትን እና ይቅር ባይነትን ገንዘባችን በማድረግ፣ መንፈሳዊ ህይወታችንን እናበለጽጋለን፡፡ አንድ ሆነን፣ በፍቅር እና በሰላም እናድጋለን፡፡ ትህትና፣ ደግነት እና ይቅር ባይነት የማይፈቱት ችግር የለም፡፡ የማያሻግሩት ወንዝ የለም፡፡
ውድ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና መላ ኢትዮጵያውያን!
ይህን ታላቁን መውሊደል ነቢ ስናከብር ለሌሎች እምነት ተከታዮች፣ ወንዱ ለሴቱ፣ ትንሹ ለትልቁ፣ በሀገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ፣ የትም ላለው ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉም ለሁሉም ትሁት ይሁን! ደግ ይሁን! በደልም ሲኖር፣ ይቅር ባይነት ይኑር!
ትህትና፣ ደግነት እና ይቅር ባይነት ብዙዎቹን ችግሮቻችንን ይፈቱልናል፡፡ ብዙ ይቅርታዎች ብዙ ርቀት ወደፊት ያራምዱናል፡፡
በየቦታው የሚነሱ አንዳንድ ችግሮችን እያየ፣ ሁሉ ነገር ጨለማ የሚመስለው ወገን አለ፡፡ ከየትኛውም ጨለማ በኋላ ግን ብርሀን አለ! ከየትኛውም ቋጥኝ እና ተራራ ባሻገር መንገድ አለ፡፡ ወንዙ፣ መሻገሪያ አለው፣ አቀበቱ ቁልቁለት አለው፡፡ ትሁት ብንሆን፣ ብርሀን ይታየናል፡፡ ደግ ብንሆን፣ መንገዱን እናገኘዋለን፡፡ ይቅር ባይ ስንሆን፣ መሻገሪያው ይታየናል፡፡
ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ነገሮችን ለማስተዋወቅ፣ መጥፎ ተግባራትን ሊቃወሙ የተሰጡ ናቸው፡፡ የሳቸውን አስተምሮ የሚከተል ሁሉ በዚህ ደረጃ ለመገኘት የሚደክም ነው፡፡ በጎ ነገሮች ተጓድለው ሲገኙ ወገኖችን ለማስተማርና ለመመለስ የሚደክም ነው፡፡
በዓሉን ስናከብር የነቢዩ መሐመድን በረከቶች በማስተዋልና የትህትና መንገዶችን በማሰብ ማሳለፍ ይገባል፡፡
በድጋሚ መልካም መውሊደል ነቢ!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ