ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከ136 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሮ እንዲሻሻል ማስቻሉን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት በእኖር፣ በእኖር ኤነር መገር እንዲሁም በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር በ17 አመታት ቆይታው ከ136 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሮ እንዲሻሻል ማስቻሉ አስታውቋል።
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በአካባቢው የነበረውን የ17 አመታት ቆይታ ማጠቃለያ መርሃ-ግብር በጉንችሬ ከተማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሄዷል።
ድርጅቱ ለህብረተሰቡ ላበረከተው አስተዋፆ ምስጋና እንደሚገባው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአካባቢው በቆየባቸው አመታት በጤና፣ በትምህርት፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ እና ሌሎችም መንግስት ተደራሽ ያላደረጋቸው የልማት ክፍተቶች በመዝጋት አስተዋፆ እንዳደረገ ገልፀዋል።
ድርጅቱ በየማህበራዊ መሰረቱ የግንዛቤ ስራ ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መብራቱ በወረዳው አሁንም የንፁህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ የሚጎዙ ፤በትምህርት ተቋማት ርቀትና በገቢ አቅም ውስንነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩ ህፃናት እንደመኖራቸው መጠን በሌሎች አማራጮች የድርጅቱ ድጋፍ እንዳይለያቸውም ጠይቀዋል።
ድርጅቱ በአካባቢው ፍሬያማ ተግባር እንዲያከናውን ሲደግፉ ለነበሩ የመንግስት ባለድርሻ አካላት፤ ለማህበረሰቡ እንዲሁም ለዎርልድ ቪዥን ኮሪያ ምስጋናቸውን ያቀርቡት ቡድን መሪው ሚስተር ስቴቨን ኮርት የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት የግድ ሀብታም መሆን እንደማይጠበቅ ይልቁንም በልበቀናነት ተጋግዞ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ወርልድ ቪዥን በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የእኖር አካባቢ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ አለሙ ዳካ እንዳሉት በሁለቱም ወረዳዎችና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ 19 ቀበሌዎች በህፃናት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራት ተከናውነዋል።
ድርጅቱ በአካባቢው በቆየባቸው 17 አመታት በተለይም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት 737 ሚሊየን ብር ኢንቨስት በማድረግ የትምህርት እድል እንዲሁም የንፁህ መጠጥ ውሃና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉን አቶ አለሙ ጠቁመው በዚህም በሁሉም ዘርፎች 136 ሺህ 737 ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
አክለውም ወርልድ ቪዥን አካባቢው ቢለቅም ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት ግን በየመዋቅሩ ያሉ የአካባቢው ባልድርሻ አካላት ባለሀብቱና መላው ማህበረሰብ ተንከባክቦ መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ሃምሳ አለቃ ነጋሽ ሁሴን እና አቶ ገሽግሽ ወርቁ የጉንችሬ ዜሮ አንድና ሻንቃ ቀበሌ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም ተጋላጭ ሴቶችና ህፃናት በመደገፍ ሲያበረክት የነበረው አስተዋፆ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።
በድርጅቱ ሲደገፉ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዮርዳኖስ አብራሃም እና ቅድስት ጎላ እንዳሉት፤ ዎርልድቪዥን ኢትዮጵያ በመማሪያ ግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
በድርጅቱ በኩል የተደረገላቸው ድጋፍም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ