በበዓላት ወቅት በሚፈጸሙ የእርድ ስነ-ስርዓት ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለመስቀል በዓል በሚፈጸመው እርድ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አሳሰበ፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከ95 ሺ በላይ ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱም ተጠቁሟል ።
ቆዳና ሌጦ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ዘርፎች መካከል አንዱ ሲሆን ምርቱን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ በእርድ ወቅት ለቆዳና ሌጦ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ በሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የእንስሳት ምርት ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ታደለ ኤርሱሎ ተናግረዋል።
እንደ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት 95 ሺህ714 ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ታደለ፥ ከዚህም ውስጥ 30 ከመቶ በመስቀል በዓል ላይ ከሚፈጸመው እርድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ቆዳን የሚረከቡ ዘጠኝ ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው ነጋዴዎች መኖራቸውንና ቆዳን በተመጣጣኝ ዋጋ በወቅቱ መረከብ እንዲችሉ የጋራ ዉይይት በማድረግ ከስምምነት መደረሱንም ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ በእርድ ወቅት ለቆዳ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ በማቅረብ ከዘርፉ እንደሀገር የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ እንዳለበትም አሳስበዋል ።
የቆዳና ሌጦ ዋጋ ዝቅ ማለቱን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ግልሰቦች በየመንገዱ እንደሚጥሉና ይህ ደግሞ ለጤና እክል የሚፈጥር በመሆኑ ህብረተሰቡ የሀገር ሀብትን ያለአግባብ መጣል እንደሌለበትም አቶ ታደለ አክለዋል።
ሀጂ ሁሴን አወል በሆሳዕና ከተማ የቆዳና ሌጦ ተረካቢ ነጋዴ ሲሆኑ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ከሚታረዱ እንስሳት የሚገኘው ቆዳና ሌጦ ለመረከብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ