ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አት ደመቀ መኮንን በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር አደረጉ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በ78ኛው የመንግስታቱ ድርጅት አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ንግግር አደረጉ።

በንግግራቸው ሃገራዊ ፣ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል።

የአረንጓዴ ልማት ስራዎች እና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን ገቢራዊ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት፣ አለምአቀፍ ሰላም እና ፀጥታ ፣ ዘላቂ ልማት ግቦች ፣ የአለም የአየር ንብረት በንግግራቸው የተዳሰሱ ጭብጦች ነበሩ።

ኢትዮጵያ የአስር አመት የልማት እቅዷን ከተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አጣጥማ በመቅረፅ እየተገበረች ትገኛለች ያሉት አቶ ደመቀ፤ የአለም አየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የተቀናጀ ስራ እያከናወነች እንደምትገኝም አንስተዋል።

እንደ አብነትም የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በማንሳት በገጠርና በከተሞች ከአካባቢ ጋር የተቆራኙ የልማት ስራዎችን በማስፋፋት ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እአአ በ2030 ለማሳካት የታቀዱትን ዘላቂ የልማት ግቦች የእስከ አሁን አፈፃፀማቸው አመርቂ አለመሆኑን የጠቀሱ ሲሆን በቀሩት ጊዜያት የተሻለ ስኬት እንዲኖር የፓለቲካ ቁርጠኝነት እና አዲስ አለም አለምአቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ ድህረ ፕሪቶሪያ ያለውን የሰላም ስምምነት አተገባበር ያነሱ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የሽግግር ፍትህን ለማረጋገጥ ፖሊሲ ተረቆ በሃገር አቀፍ ደረጃ ምክክር እንደተደረገ የጠቀሱ ሲሆን እርቅ ፣ እውነትን ለማፈላለግ እና ተጠያቂነትን እውን ለማድረግ መንግስት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ የአለም አየር ንብረት ለውጥ በአዳጊ ሃገራት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት እስከ 2030 ድረስ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የተቀመጠው እቅድ እየተሳካ እንዳልሆነ አንስተዋል።

በቀጣይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚካሄደው የአለም አየር ንብረት ጉባኤ ሃገራት ተግባራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለተልዕኮው ስኬታማነት ተቋማዊ ማሻሻያን ማድረግ አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ ነው ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን አቶ ደመቀ የገለፁ ሲሆን ፤ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀጫ እንዲኖራትም በአህጉር ደረጃ የተያዘው አቋሞ ተገቢነትን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም እና ልማት ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ አጠናክራ የማስቀጠል ፍላጎት እንዳላት ያነሱ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗንም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢው ሃገራት ዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዝ ተምሳሌታዊ የልማት ፕሮጀክት እንደሆነም አቶ ደመቀ መኮንን አንስተዋል።