በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ልማት ጽ/ቤት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልገሎት ሥራ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ልማት ጽ/ቤት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልገሎት ሥራ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጿል፡፡

የበጎነትን ሥራ ለወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥል ጽ/ቤቱ አረጋግጧል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር  መንገድና ትራንስፖርት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምራየሁ አድማሱ በ2015 ዓ.ም ላይ ጽ/ቤታቸው የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣታቸውን ተናግረዋል።

የአቅመ ደካማና የዘማች ቤተሰብ ቤት ግንባታ፣   የትምህርት ጥራትን የሚያግዙ  የተማሪዎች መቀመጫ ጥገና፣ አሰፋልት መንገድ ላይ ዜብራ መቀባትን  ጨምሮ በሌሎች ስምንት  ተግባራት ላይ አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል።

በዚሁ በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ጽ/ቤታቸው ማህበረሰቡን በማስተባበር ባከናወናቸው ተግባራት ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚሆን ውጭ ከመንግሥት ካዝና ይወጣ የነበረውን ማዳን መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል።

የትራፊክ አደጋ መከላከል በሚቻል ሁኔታ ላይ ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ  የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራታቸውን ተናግረዋል።

በ2014 ዓመት ላይ በበጎ ፊቃድ አገልግሎት በሠሩት ተግባራት ከዞኑ የዋንጫ ተሸላሚ  እንደነበሩም ያስታወሱት አቶ ታምራየሁ በጎነት ከንፁህ ህሊና የሚመነጭ ተግባር በመሆኑ ለወደፊትም  አጠናከረው እንደሚቀጥሉ አሰረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ተሰፋዬ ጎበና – ከፍስሃ ገነት ጣቢያችን