የመስቀል በዓልን ለልማትና ለዕርቅ ከማዋል ባሻገር አንድነታችንን የምናጠናክርበት በዓል ልናደርገው ይገባል  –  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና ኤዢያና ፓስፊክ አገሮች ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር ገበዬሁ ጋንጋ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመስቀል በዓልን ለልማትና ለዕርቅ ከማዋል ባሻገር አንድነታችንን የምናጠናክርበት በዓል ልናደርገው ይገባል ሲሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና ኤዢያና ፓስፊክ አገሮች ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር ገበዬሁ ጋንጋ ገለፁ።

የእርቅና የሰላም በዓል የሆነው የዘይሴ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ቡዶ ኬሶ” በጋሞ ዞን ዘይሴ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ የይገኛል።

በጋሞ ዞን ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል የዜይሴ ብሔረሰብ በደማቅ ሁኔታ የሚያከብረው የ “ቡዶ ኬሶ ” የዘመን መለወጫ መስቀል በዓል በዘይሴ ኤልጎ ተከብሯል።

የዘይሴ ብሔረሰብ ሀገር ሽማግሌዎች በምረቃ በማድረግ በዓሉን አስጀምረዋል።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፊሬ እንኳን ለዘይሴ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቡዶ ኬሶ ” በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለው በዓሉ የተራራቁ የሚገናኙበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ያዘነ  የሚፅናኑበት፣  ልዩነትን የሚቀርበትና አንድነት የሚነግስበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን በማልማትና  ለቱሪዝም ሀብት እንዲውል ማድረግ ቀጣይ ተግባራችን ነው ያሉት አስተዳዳሪው እጅ ለዕጅ ተያይዘን አከባቢውን በማልማት የተጀመረውን የልማት ጉዞ ማስቀጠል የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ  አቶ አባይነህ አበራ በጋሞ ዞን የጋሞ፣ ዘይሴና ጊዲቾ ብሔረሰቦች ዘመናትን በአብሮነትና በመተሳሰብ መቆየታቸውን ጠቁመው ለብሔረሰቡ ተወላጆችና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

አቶ አባይነህ አክለው የዘይሴ ብሔረሰብ ቋንቋውን፣ ባህሉን እና ማንነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ማንኛውንም እንቅስቃሴ የጋሞ ዞን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የኤዢያና ፓስፒክ አገሮች ዳይሮክተሬት ጄነራል ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ገበየሁ ጋንጋ የዘይሴ ብሔረሰብን አንድነት ከማጠናከር ባሻገር እሴቱን መጠበቅ ከሁሉም የሚጠበቅ ሀላፊነት መሆኑን ገልፀው በትምህርት ጥራት ላይም መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በበዓሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የኤዢያና ፓስፒክ አገሮች ዳይሮክተሬት ጄነራል አምባሳደር ዶ/ር ገበየሁ ጋንጋን ጨምሮ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአከባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።

በቡዶ ኬሶ በዓል ላይ በብሔረሰቡ ባህል ላይ ትኩረት ያደረገ “ዳንዱባ” የተሰኘ የብሔረሰቡ የስነ ቃል መፅሀፍ  በአቶ መሳይ ደምሴ ተዘጋጅቶ ተመርቋል።

በበዓሉ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በዓሉ ዳመራ በመደመር ፍፃሜ አግኝቷል።

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን