የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአሪ ዞን ዎባ አሪ ወረዳ ለሚገኙ ወላጅ አጥና አቅመ ደካማ ቤተሰብ ላላቸው ህፃናት የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአሪ ዞን ዎባ አሪ ወረዳ ለሚገኙ ወላጅ አጥና አቅመ ደካማ ቤተሰብ ላላቸው ህፃናት የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸዉ ተማሪዎች ድጋፉ ከትምህርት ገበታ  እንዳያቋርጡ በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸዉን ገልፀዋል።

ድጋፉን ከተቀበሉት በወረዳው የዲራመር ቀበሌ ነዋሪ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አበራ ጋፂ፣ ጤማቲዮስ ሩጫና ወሳኙ ሩጫ በጋራ በሰጡት አስተያየት ወላጅ አባቶቻቸዉን በሞት ያጡና ከእናቶቻቸው ጋር በተለያዩ ችግር ውስጥ እያለፉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎቹ አክለው አሁን ላይ እንደሀገር ከሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የመማሪያ ግበዓቶችን ባላቸው አቅም መግዛት ስላልቻሉ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ተስፋ እንዳልነበራቸው አመላክተው አሁን ላይ በተደረገላቸው ድጋፍ ተስፋቸው መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ ድጋፉን ያደሩጉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡

ወላጅ እናቶቻቸዉ ወ/ሮ ብድር ቸኮሌ፣ አልቃያ  ጋማሽች እና ሌሎች የድጋፉ ተጠቃሚዎች እንደገለፁት ምንም ዓይነት ገቢ የለላቸዉና በዝቅተኛ ኑሮ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ካለው የኑሮ ውድነት የተነሳ ልጆቻቸዉን መመገብና ማልበስ ያልቻሉ መሆናቸዉን ጠቁመዉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለልጆቻቸዉ ያደረጉትን የትምህርት ግበዓት ድጋፍ የነበረባቸውን የኑሮ ጫና እንዳቀለለላቸው ተናግረዋል፡፡

የዎባ አሪ ወረዳ ትምህርተ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ እምቢያለው አበራ እንደገለፁት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአከባቢዉን ህብረተሰብን ማህበራዊ ችግሮች ላይ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ በርካታ የወረዳው ችግር መቀረፉን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ከሚያደርገው የመማሪያ ግበዓት በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በወረዳው ላሉ ትምህርት ቤቶች ኮፒተር፣ የተለያዩ የጽህፈት መሣሪያዎችንና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ እንደምገኝ ኃላፊዉ አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለ2016 የትምህርት ዘመን በወረዳው ላሉ ወላጅ አጥና አቅመ ደካማ ቤተሰብ ህፃናት ደብተር እና እስክሪብቶ ድጋፍ ማድረጉን አቶ እምብያለው ተናግረዋል፡፡  

ዘጋቢ፡ መላኩ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን