የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ምርታማነትን በማሳደግና ጥራቱን በማሻሻል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አሳሰበ
ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ምርታማነትን በማሳደግና ጥራቱን በማሻሻል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ሲል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አሳስቧል።
“ባለስልጣኑ የቡና ምርት ጥራት ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ሀሳብ በቡናና ቅመማ ቅመም ምርትና ጥራት ላይ ያተኮረ ውይይት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬን ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ቡና ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝና ለሀገር ኢኮኖሚም የጀርባ አጥንት በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጸኦ የላቀ መሆኑ በዘርፉ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ይናገራሉ ።
ለአብነትም ባሳለፍነው በጀት አመት በሀገር ደረጃ ከተመዘገበው ገቢ ከቡና ምርት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን ከምርት ጥራት ጉድለት የተነሳ በአለም ገበያ ፍላጎት ማነስና መሰል ችግሮች የተፈለገው ውጤት እንዳይሳካ ማነቆ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ቡናን በብዛት እና በጥራት በማምረት ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በትጋት መስራት አለበት ብለዋል።
እንደክልል የቡና ሽፋን 560 ሺህ ሄክታር አካባቢ ማድረስ መቻሉን የገለጹት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዮሐንስ መላኩ ለሃገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ቡና ሻይ ቅጠልና ሌሎችም የቅመማ ቅመም ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት ክልል መሆኑን ገልጸዋል።
ባሳለፍነው በጀት ዓመት 64 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለመቅረብ ታቅዶ 42 ሺህ ቶን ማሳካት መቻሉን የገለጹት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይ ኩጁአብ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለቡና ግብይት ሥርዓት መዘመን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊዎች ሲሆኑ ህገ-ወጥ የቡና ግብይትና መሰል ችግሮች እንዲታረሙ አስፈላጊው ክትትል ሊደረግ ይገባል በማለት አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የቡና ሰርተፍኬሽን ማዕከል በአቅራቢያቸው እንዲከፈት እቅድ መያዙ ከዚህ ቀደም የነበረውን እንግልት የሚቀንስላቸው መሆኑን ተሳታፊዎቹ አክለዋል፡፡
ቡናን በስፋትና በጥራት ለማምረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከባለፈው አመት ጀምሮ ሰፊ የንቅናቄ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያ
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ