ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የካፈቾ ብሔር “የሜኔ ሻዴ ባሮ” የብሔረሰቡን ማህበራዊ ትስስር ከማጠናከር አንጻር የነበረዉ ሚና የጎላ እንደነበር የካፋ ዞን አስተዳደር ገለጸ።
የብሔረሰቡ የ2016 ዓመተ ምህረት ዘመን መለወጫ በዓል በቦንጋ ከተማ በፓናል ዉይይትና በሌሎች ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ መከበር ጀምሯል።
የበዓሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዓሉ የካፈቾ ብሔረሰብ አዝመራን ማጠናቀቁን ተከትሎ ሲከበር የቆየ ነዉ ብለዋል።
ይሄው የዘመን አቆጣጠር ከገበሬው የእርሻ አመራረት ባህል እና ልማድ ጋር ተያይዞ ከሃምሌ አንድ ጀምሮ 77 ቀናት ተቆጥረውና በመስከረም 12 እና 13 የካፈቾ ዘመን መለወጫ ተደርጎ ከ750 ዓመታት ፊት ጀምሮ በቀደምት አባቶቻችን ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የተጋጩ አካላት እርስ በእርስ ይቅር የሚባባሉበት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተከናወኑ ተግባራትም የሚገመገሙበት ስርዓት እንደነበርም ገልጸዋል።
ይህ የካፈቾ ብሔረሰብ መገለጫ የሆነዉ በዓል ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለመጪው ትዉልድ እንዲተላለፍና በዓለም የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) መዝገብ ዉስጥ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የዞኑ አስተዳደር በትኩረት ይሰራልም ብለዋል አቶ እንዳሻዉ።
በዓሉ ለ120 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከበር ተቋርጦ መቆየቱን አስታዉሰዉ አሁን ታሪካችንን በሚመጥን መልኩ መከበር እንዲችልና የቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆንም ይሰራል ብለዋል።
በዓሉ በዛሬዉ ዕለት በፓናል ዉይይትና የተለያዩ ፌስቲቫሎች የሚከበር ሲሆን በነገዉ ዕለትም በቦንጌ ሻምቤቶ የጮንጌ ስነስርዓት ይከወናል።
በክብረ በዓሉ የምክሬቾ አባላት፣ የፌዴራል ምክር ቤት አካላት፣ ከተለያዩ አጎራባች ዞኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ከአጠቃላይ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እያከበሩ ነዉ።
ዘጋቢ: አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ