በግንባታ ሂደት ላይ ላሉ የጤና ተቋማት ተገቢው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በግንባታ ሂደት ላይ ላሉ የጤና ተቋማት ተገቢው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ ዋካ ከተማ እየተገነባ ያለውን ሆስፒታል የግንባታ ሂደቱን አስመልክቶ የአከባቢው ነዎሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጎብኝተዋል፡፡
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ ዋካ ከተማ እየተገነባ ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ሂደቱ አሁን በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
የግንባታ ሂደቱን አስመልክቶ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በስፍራዉ በመገኘት የጎበኙት ሲሆን የሆስፒታሉ ግንባታ ስራም ወደ 90% ከአጠቃላዩ የተገባደደለት መሆኑ በዚህን ወቅት ተገልጿል።
የግንባታ ስራውን አሁን ባለው ምዕራፍ በመረከብ የጌታቸው ጠቅላላ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ድርጅት እየገነባ ያለ ሲሆን የድርጅቱ ባለቤትና የስራው ተቋራጭ የሆኑት አቶ ጌታቸው አባተም በዚህን ወቅት ሥራውን አጠናቀው ለማስረከብ የሁለት ወይንም የሦስት ወራት ጊዜ ብቻ ሊፈጅ ይችላል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን ግንባታውን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ገንዘብ ክፍያ ወቅቱን ጠብቆ ያለመከፈልና የግንባታ ቁሳቁሶችን ለማስገባ በአካባቢው ያለው መንገድ ምቹ ያለመሆኑን እንደተግዳሮት አንስተዋል።
የማረቃ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነም በዚህን ወቅት ሆስፒታሉ የደረሰበት የግንባታ ደረጃ የሚያስመስግን መሆኑን በመጥቀስ ሥራው ግን በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሲሉ አያይዘው አሳስበዋል።
ለዚሁም ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ አካላት የአከባቢውን ህብረተሰብ ጨምሮ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሲሉ ጠይቀዋል።
የዳውሮ ዞን ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ኦሞሼም በበኩላቸው የሆስፒታሉ የግንባታ ሂደት በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል አንደባለድርሻ አካል ከዞኑ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተቋራጩ በግንባታ ሂደቱ ተግዳሮቶች ናቸው ሲሉ ላነሷቸው ችግሮችም የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ እንዲሰጡ ለማስቻል የበኩላቸውን ጥረት በተጨማሪም እንደሚያደርጉ አስታውቋል።
በጉብኝቱ ላይ ከአከባቢው የተወጣጡ ነዋሪዎችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ከየደረጃው የተገኙ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች የተገኙበት ሲሆን አንዳንዶቹም በሰጡት አስተያየት ግንባታው አሁን ለደረሰበት ደረጃ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በሂደቱ በተመሳሳይ ለሚያስፈልገው እገዛና ድጋፍ እንዲሁ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ