የካፋ ልማት ማህበር ከትምህርት ገበታቸዉ ወደ ኋላ የቀሩ ተማሪዎችን ለማስቀጠል የሚያስችል ሥራ እያከናወነ ይገኛል

የካፋ ልማት ማህበር ከትምህርት ገበታቸዉ ወደ ኋላ የቀሩ ተማሪዎችን ለማስቀጠል የሚያስችል ሥራ እያከናወነ ይገኛል

ሀዋሳ፡ መስከረም 09/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ከትምህርት ገበታቸዉ ወደ ኋላ የቀሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የሚያስችል ሥራ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

“ማህበሩ ጄኔቫ ግሎባል” ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር በካፋ ዞን በተመረጡ 10 ትምህርት ቤቶች የተፋጠነ ትምህርት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።

በልማት ማህበሩ የጄኔቫ ግሎባል ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ገዛኢ ተወልደብርሃን ልማት ማህበሩ በዞኑ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ወደ ኋላ የቀሩ ተማሪዎችን በመለየት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ጠሎና አዲያ ወረዳዎች ከትምህርት ገበታቸዉ የቀሩ 320 የመንጃ ጎሳ አባላትን በመለየትና ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ትምህርታቸዉን መቀጠል እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የተማሪዎቹ ወላጅ እናቶች ያለባቸዉን ጫና በመለየት ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸዉን መፍታት እንዲችሉ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የዕለት ገቢያቸዉን በሚያሳድጉባቸዉ መስኮች ማሰማራት እንደተቻለም ተናግረዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን የተፋጠነ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከጀኔቫ ግሎባል ኢትዮጵያ ጋር በተሰራዉ ስራ ከዞኑ በተለዩ ሁለት ወረዳዎች በ5 ትምህርት ቤቶች 180 ተማሪዎችን በተፋጠነ ትምህርት በ10 ወር ዉስጥ ከ1ኛ ክፍል እስከ 4 ክፍል ማሸጋገር ተችሏልም ብለዋል።

ዘንድሮ ዉጤታማነቱ ታይቶ የትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ 10 በማሳደግ 360 ተማሪዎችን ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናገረዉ በቦንጋ ከተማ ከተለዩ 7 ትምህርት ቤቶች መካከል ከፍሎቹ ምዝገባ ያላጠናቀቁ መሆናቸዉን ገልጸዋል።

የተፋጠነ ትምህርት እንደ ሀገር በ 5 ክልሎች ብቻ የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገዛኢ የዕድሉ ተጠቃሚ ተማሪዎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸዉ የተለዩና የትምህርት ወጪያቸዉ ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ የሚሸፈንላቸው ናቸው ብለዋል።

ትምህርቱ እንዲሰጥባቸዉ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለመማሪያ የሚሆኑ ቦታዎችን ከመለየት ጀምሮ ምቹ አካባቢዎችን በመፍጠር ተማሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ኃላፊነታቸዉን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

አሁን ላይ ልማት ማህበሩ የመማር ማስተማር ስራዉን ማከናዉን የሚችሉ 10 መምህራንን ቀጥሮ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዉ ምዝገባ ባልተጠናቀቀባቸዉ አካባቢዎች መቆራረጥ እንዳይፈጠር ማህበረሰቡ ችግርተኛ ተማሪዎችን እየለየ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲያስተባብር መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ-ከቦንጋ ጣቢያችን