የወርልድ ብራይት ተቋም የትምህርቱን ዘርፉን በማዘመን የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

የወርልድ ብራይት ተቋም የትምህርቱን ዘርፉን በማዘመን የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርቱን ዘርፍ በማዘመን የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የወርልድ ብራይት ተቋም ገለፀ

ተቋሙ በሆሳዕና ከተማ አዲስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት የመማር ማስተማር ስራ በይፋ ጀምሯል።

በሆሳዕና ከተማ አዲስ በተከፈተው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትምህርት ዘመኑ ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር በሰው ኃይልና የትምህርት ግብዓትን በበቂ ሁኔታ በማሟላት የትምህርት ዘመኑን ማስጀመር ተችሏል ያሉት የወርልድ ብራይት ተቋም ፕሬዝዳንት ዕጩ ዶክተር ተሰማ አበራ ናቸው።

በአዕምሮ የበለፀገና በዕውቀት የዳበረ ጠንካራ የሀገር ተረካቢ ዜጋ ከማፍራት አንፃር ተቋሙ በተለያዩ መስኮች በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ያስረዱት ፕሬዝዳንቱ ተማሪዎችም የትምህርት ጊዜያቸውን በተገቢው መልክ በመጠቀም ስኬታማ ዜጎች መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ መንግስት ያስቀመጠውን ስታንዳርድ ለማሟላት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ዶ/ር ተሰማ።

ተቋማቸው በማህበረሰቡ የትምህርት ህይወት ላይ አዎንታዊ አስተዋዕፆ ከማበርከቱ በተጨማሪ ለመማር ፍላጎት እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ዕድሉን ላላገኙ ዜጎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ሚና በተገቢው መንገድ እየተወጡ እንደሚገኙ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ለተስተዋለው ውድቀት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመለየት ለ2016 የትምህርት ዘመን እንዳይቀጥል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ በሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ የት/ቤት መሻሻልና ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ደገፈ ኤርጡሞ ናቸው።

በት/ቤቶች ሰፊ ጉድለት የነበረውን የግብዓትና የመሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታትና በአዲስ መልክ እንዲደርጁ ከማድረግ ባለፈ ስታዳርዳቸውን የጠበቁ አዳዲስ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ ተገቢውን ድጋፍ እየሰጡ ስለመሆናቸው አቶ ደገፈ ገልፀዋል።

በወርልድ ብራይት ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር ፀደቀ ነጋሽና የፊዚክስ መምህር አማረኝ ካሳዬ እንደተናገሩት በመንግስት የተወሰነውን አዲሱን የስርዓተ ትምህርት ሂደት ለተማሪዎች ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ከተቋሙ ጋር በመግባባት ወደ መማር ማስተማር ስራ መግባታቸውን አንስተዋል።

ተማሪዎችም በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ወደላቀ ደረጃ ለመሸጋገር ከውስጥ ተነሳሽነታቸው በተጓዳኝ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መልካም ስነ ምግባርን የተከተለ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ከፍተኛ የመማር ማስተማር ልምድ ያላቸውን መምህራን በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ማግኘታቸው ላቅ ያለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችላቸው የት/ቤቱ ተማሪዎች ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን