መስከረም -የፌሽታ ወር
የተጀመረው 2016 ዓ.ም አዲሱ አመት የመስከረም ወር አምና አልፎ ዘንድሮ ማለት የሚጀመርበት ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፌሽታ እና የደስታ ወር ነው።
የአመቱ የመጀመሪያ ወር በመሆኑም ልዩ ስሜት አለው። በኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር መስከረም 1 በዘመን መለወጫ በአል ሲደምቅ የወሩ አጋማሽ ቀናት ደግሞ በአደባባይ በዓላት ያሸበርቃል።
ይህ ወቅት በሀገራችን በበርካታ ህዝቦች ዘንድ በተለይ ደግሞ የደቡብ እና የማዕከላዊ እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች የመስከረምን ወር አጋማሽ በጉጉት ነው የሚጠብቁት ።
በዓላቱ ባህላዊ እሴት ተላብሶ የአዲስ አመት መቀበያ መሆናቸው ልዩ ስሜት አለው። አሮጌውን ተሰናባች አመት በመሸኘት ተናፋቂውን አዲስ አመት ግባልኝ በሞቴ የሚባልበት ወር ነው።
ዘመድ አዝማድ እና ቤተሰብ የሚገናኝበት እርቀ ሰላም ወርዶ ፍቅር የሚነግስበት ነው።
የጋሞ ህዝቦች ”ዮ መስቀላን” አመቱን በሙሉ በናፍቆት ነው የሚጠብቁት።በጎረቤት ጎፋም ” የጋዜ መስቀላ” ተመሳሳይ ስሜት ያለው ነው።
በወላይታ ጊፋታ ልዩ ቀለም አለው ። ጊፋታ በመቶ ሺህ የሚገመቱ ተሳታፊዎችን በፍቅር በአንድ አደባባይ ያውላል።
በየም ” ሄቦ ” ም ቀደም ብሎ በሚደረግ ቅድመ ዝግጅች እስከ ጥቅምት 5 በአደባባይ ይከበራል ።
ተናፋቂው የመስቀል በዓል በጉራጌዎች ዘንድ ልዩ ቦታ አለው። የጉራጌዎች ልዩ የመስቀል አከባበር የመላው ኢትዮጵያውያን ቀልብ የሚስብ በመሆኑ በርካታዎች የጉራጌ ተወላጆችን በመከተል ወደ ጉራጌ ይታደማሉ።
ለሀዲያ ህዝብ ”ያሆዴ” አዲስ አመት መቀበያው እና ፈጣሪን ማመስገኛው ነው።
በከምባታ አከባቢ ደግሞ ”ማሳላ” ተመሳሳይ እሳቤ ፣ አከባበር እንዲሁም ድምቀት አለው።
የከፊቾ ፣ የጠምባሮ ፣ የዘይሴ”ቡዶ ኬሶ” የግዲቾ”ባላ ካዳቤ” የዶንጋ የሸካና ከሌሎች ህዝቦች ጋር ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ወቅት ነው የሚከበረው ።
የሁሉም በዓላት መነሻቸውም መድረሻውንም ከጨለማው ክረምት ወደ ፈካው ፀደይ መሸጋገርን ማብሰርን ነው። ሰላምና ፍቅር ፣ አብሮነትን እና ህብራዊነትን ማስፈን ነው። ቤተሰብን ማህበረሰብን፣ህብረተሰብን እና ህዝቦችን በፍቅር ማስተሳሰር ነው።
የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅትም በደቡብ እና በማዕከላዊ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ሰሞኑን አዲስ አመታቸውን ለሚቀበሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መልካም አዲስ አመት ይመኛል ።
አዘጋጅ ፡ ጀማል የሱፍ
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ