ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን መስጠቱን ገለጸ

ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን መስጠቱን ገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ::

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታምራት ታገሰ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ስራዎችን በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በጤና፣ በግብርና፣ በሕግና በትምህርት አገልግሎትና በተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ ዘርፎች ላይ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በማስተርስ ዲግር ተማሪዎች ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን ማስቆፈር መቻሉን የተናገሩት ዶክተር ታምራት በሆሳዕና ከተማ የውሃ እጥረት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

በትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ያጋጠመውን የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን የሚጠይቅ ነው ያሉት ዶክተር ታምራት በሀድያ፣ በከምባታ፣ በሀላባ ዞኖች እና ጠምባሮ ልዩ ወረዳ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ግንባር ቀደም ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርቶችን ከዞንና ከወረዳ የፈጠራ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረጉን አስረድተዋል ዶክተር ታምራት፡፡

በጤና ዘርፍም በዞኑ የሚገኘውን የንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጊዜውን የሚመጥኑ የተለያዩ ዘመናዊ ማሽኖችን በማስመጣት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል::

ከዚህ በተጨሪ በሆሳዕና ከተማና አካባቢው ለሚኖሩና ለተያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና በተለይም የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በስፋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የግብርና ጥናትና ምርምር የሚሰራባቸው ሰባት ማዕከላት መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ታምራት በከብት፣ በእንሰት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡናና በተለያዩ የችግኝ ዝርያዎች ጥናትና ምርምር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀዲያ ዞን የሚስተዋለውን የእንሰት አጠውልግ በሽታን ችግር በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል ጥናትና ምርምር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡

በተጨማሪም የተለያየ ጠቃሜታ ያላቸውና በምርምር ማዕከል የተረጋገጡ ችግኞችን በማዘጋጀት ለወረዳዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለተለያዩ ዜጎች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ በቡና አብቃይ አካባቢ ለሚገኙ አርሶአደሮች ምርታማ የሆኑ የቡና እና የአፕል ችግኞችን ለአርሶአደሮች ማከፋፈሉን ዶክተር ታምራት ገልጸዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን ከመማር ማስተማር ስራ በተጨማሪ በርካታ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናወኑም አስታውቀዋል::

ዘጋቢ፡ በየነ ሰላሙ- ከሆሳዕና ጣቢያችን