በግ በፔስል
አንዳንዴ አውደዓመት ሲመጣ አይረሴ ገጠመኝና ትዝታው ጓዙን ጠቅልሎ ከተፍ ይላል። የበዓላት ድምቀት አንዱ ገጽታቸው አንዳች አይረሴ ክስተቶችን ጥለው ማለፋቸው። በሀገራችን የተለያዩ በአላትን ስናከብር እንደየበዓሉ አይነት የሚደረገው ዝግጅት እንደ ሰዉ አቅም ቢሆንም÷ ቅሉ ግን ሁሉም ሰው ቤቱ ያፈራውን እንደየአቅሙ ማሰናዳቱ አይቀሬ ነው። ታዲያ የበዓሉ ትዝታ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። ከወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ አውደአመትን በጥሩ ትዝታ ለማሳለፍ ቀድሞ በሚደረገው ዝግጅት መሐል የሚፈጠሩ ጥሩም ሆኑ መጥፎ ነገሮች በዓል በመጣ ቁጥር መታወሳቸው አይቀርም።
ለአውደአመቱ በምናደርገው ዝግጅትና በእለቱ የሚገጥሙን ገጠመኞች ያልታሰበ ይሆንና በአል በመጣ ቁጥር ትዝ ማለቱ የግድ ይሆናል። ታዲያ በዚሁ ጊዜ አንድ ወዳጄ ለበዓሉ ድምቀት በሚያደርገው ዝግጅት መሐል የገጠመውን ሁኔታ ሳስታውሰው ሁሌም ፈገግ ያደርገኛል። ነገሩ እንዲህ ነወ፦
አቶ አብርሐም ይባላል የመንግስት ተቀጣሪ ሾፌር ነው፡፡ ከሀዋሳ ወደ ዳውሮ ለስራ ጉዳይ እሱን ጨምሮ ከ4 ባለሙያዎች ጋር ጉዞ ያደርጋሉ፡፡
ዳውሮ ታርጫ ከተማ ደርሰው ለዕለቱ የነበራቸውን ስራ አጠናቀው ወደ ማደሪያቸው የነገ ሰው ይበለን ተባባለው ይለያያሉ፡፡
በነጋታው ጠዋት ሾፌሩ ይዟቸው ከሄደው ባልደረባው አንዱ ጠርቶ፥ ማታ ወንድሜ ደውሎ ለበዓል መዋያ የሚሆን ገንዘብ በባንክ ልኮልኛል እባክህን እዚህ ሀገር በግ እርካሽ ስለሆነ ገዝቼ ለቤተሰቦቼ ይዤ ልሂድ ይለዋል፡፡ ከዚያም ሹፌሩ መስማማቱን ገልጾለት ብሩን ከባንክ አወጡና በግ የሚሸጥበት አካባቢ አለ የተባልንበት ቦታ ሄደዉ በጉን ገዙ፡፡ ባልደረባዬ እጅግ በጣም ተደሰተ፡፡ ለባለቤቱና ለልጁ ደውሎ በግ መግዛቱን ነገራቸው፡፡ በጊዜው እነሱም ደስተኞች ነበሩ፡፡
ከዚያም ስራችንን ጨርሰን የመልስ ጉዞ ወደ ሀዋሳ ተጀመረ፡፡ ነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው እንግዲህ፡፡
መንገድ ላይ እንጨት ሲገኝ እባክህ በዓል ነው ገዝተን እንድንጭን ፍቀድልን የሚሉ ሌሎች ባልደረቦች ጥያቄ ለሾፌሩ አቀረቡ፡፡ ሾፌሩም ፈቀደና እንጨትና ከሰል ገዝተው መኪናው ላይ ጫኑ፡፡ በዚያ ጊዜ ተመቻችቶ ታስሮ የነበረው በግ ከእንጨቱና ከከሰሉ በላይ ከፍ ብሎ እንደታሰረ ተቀመጠ፡፡
የበጉም ባለቤት የበጉን አቀማመጥና መታሰሩን በደንብ ካረጋገጠ በኋላ ጉዞ ቀጠልን፡፡
በጉዞ ላይ እያለን በመካከል ተራ በተራ እየወጣን የበጉን ደህንነት በማረጋገጥ እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሂደት ላይ እያለን ወላይታ ሶዶ መግቢያ አካባቢ እንደደረስን በጉ ከመኪናው ላይ ዘሎ ወረደ፡፡ የዚያን ጊዜ ሁላችንም ከመኪና ወርደን የበጉን ሁኔታ ስንመለከት ጭንቅላቱ በድንጋይ ተመትቶ ወድቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ነፍሱ አልወጣችም፡፡ በአካባቢው የነበሩ አርሶ አደሮች በጉ እንደማይተርፍ ሲረዱ ቢላዋ አምጥተው በህይወት እያለ እረዱት ማለት ጀመሩ፡፡ አርሶ አደሮቹ በጉን በነፍስ እያለ ባርከን ስላረድን ችግር የለውም ስጋውን ይዛችሁ ሂዱ ብለው ለባለበጉ ባለቤት አስረከቡ፡፡
የበጉ ባለቤት እጅግ አዘነና ለባለቤቱና ለልጁ ትልቅ በግ እንደገዛና ይባስ ብሎ በስልክ ለልጁ የበጉን ድምፅ ያሰማ እንደነበር ሲያስበው፥ አሁን እንዴት አሳርጄ በግ በፔስታል ይዤ ሄዳለሁ? ሲል ተበሳጨ! የተሰማውን ሁሉ ተናገረና ለአርሶ አደሮቹ ስጋውን ይዞ መሄድ እንደማይፈልግና እነሱ እንዲጠቀሙ ሰጥቷቸው ወደመኪናው ገባ፡፡
በተፈጠረው ነገር ሁላችንም አዝነናል፤ በጣም ደንግጠናል፡፡ መኪና ውስጥ የነበረው ሳቅና ጨዋታ ወደ ፀጥታ ተቀየረ፡፡ የበጉ ባለቤት አሁን ምንም አይነት ወሬ አልፈልግም አለ፡፡ ማጽናናትም አልቻልንም፤ እንዲሁ እንደተዘጋጋን ከወላይታ ሶዶ ሀዋሳ ገባን ሲል ሾፌራችን የበዓል ገጠመኙን አጫወተን፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፥ የበዓል ሰሞን ገጠመኙ አይነተ ብዙ ነውና አንድ ሌላ እህታችን ያጋራችንን ገጠመኝ ላካፍላችሁ። ወ/ሮ ገነት ቡፌቦ ትባላለች፡፡ የገና በዓል ከቤተሰቦቼ እንዲሁም ከወዳጆቻችን ጋር ደስ በሚል ሁኔታ አሳልፈን ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ሆነ፡፡
ከዚያም ለባለቤቴና ለልጆቼ እራት አቅርበን እየበላን እያለ በሰፈራችን የጩኸት ድምፅ ከውጪ ሲሰማ ባለቤቴ የሚባላውን ምግብ ትቶ ሁለት ሰዎች ሲደባደቡ ደረሰ፡፡ ነገር ግን የሚደባደቡበት ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ሰክረው ነው፡፡ ከዚያም ባለቤቴ በመካከላቸው ገብቶ ለመገላገል ሲሞክር ሲጣሉ የነበሩ ሁለቱ ጓደኛሞች ባለቤቴን ክፉኛ ደበደቡት፡፡
በዚህ መካከል በቦክስ የተመታበት ከንፈሩ ተሰንጥቶ ይደማ ነበር፡፡ ባለቤቴ ፊቱ ደም በደም ስለነበር ጮኩኝና ሰዎች ተሰበሰቡ ትላለች ወ/ሮ ገነት፡፡
ከዚያም የአካባቢ ሰዎች ተደባዳቢዎቹንና ባለቤቴን ይዘው ፖሊስ ጣቢያ አደረሱን፡፡ በሰዓቱ የነበሩ ፖሊሶች በስካር መንፈስ እንደሆኑ ስለተረዱ አስታረቁንና ደብዳቢዎቹ ይቅርታ ጠይቀው እኛም ወደቤታችን ተመለስን፡፡
ወ/ሮ ገነት ስትናገር ቀደም ሲል የጀመሩትን እራት እንደገና አቀረብን፡፡ ይሁንና ባለቤቴ የላይ ከንፈሩ ተሰንጥቆ ደም ይፈሰው ስለነበር በወቅቱ መብላት አልቻለም፡፡
እንግዲህ በእነዚህ ገጠመኞች ብዙ የተማርን ይመስለኛል፡፡ በበዓላት ወቅት የምናከናውናቸውን ነገሮች ጥንቃቄና ብልሃትን ይፈልጋሉ፤ የበዓል ደስታችንን የሚቀማን ነገር እንዳይኖር ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል። እናንተም የተለያየ የበዓል ሰሞን ገጠመኞቻችሁን በኮሜንት መስጫው ላይ ብታጋሩን በማለት ደሬቴድ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንልዎ ይመኛል፡፡
ዘጋቢ፡ ሐና በቀለ
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ