2015 ዓ.ም አምና ተብሎ ሊጠናቀቅ የአንድ ቀን ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ ብዙ ደግና ክፉ ነገር ባስተናግድንበት 2015 እንደሀገር ነገን በተሻለ ተስፋ ማሰብ የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡ እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነገሮች በተፈጸሙበት፣ በርካታ በጎና አስደሳች ነገሮች በተሰሙበት፣ ብዙዎችን ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ የከተቱ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች የተስተናገዱበት አመት 2015፤ የአገራችን መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው ከዘገቧቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የተወሰኑትን መራርጠን እነሆ ብለናል፡፡
ብዙሃኑን ለጥፋት የዳረገው የሰሜኑ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ያገኘው ሊጠናቀቅ ቀናት በቀረው 2015 ዓ.ም ነበር፡፡ በተለይ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሃዲድ ቅርጹን እንደቀየረ በብዙ ይነገራል፡፡ የሰላም ስምምነቱ፥ የሰላምና የአህጉራዊ ዲፕሎማሲ የበላይነት የተመዘገበበት እና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ችግሮችን በራስ የውስጥ አቅም መፍታትና መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻል ግልጽ ትምህርት የሰጠችበት አመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በሰሜኑ ግጭት ምክንያት ፈተና ገጥሞት የነበረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፥ በተለይም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከዳር መድረሱና የተፈረመው የሰላም ስምምነት የመቀልበስ አደጋም ሳያጋጥመው መፈጸም መቻሉ አመቱን በልዩነት እንዲታወስ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የብሔራዊ ጥቅምን መርህ ጠብቆ የሚፈጸሙ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶች የዲፕሎማሲ ስኬት የተገኘበት አመት ሆኖ አልፏል፡፡
ኢትዮጵያ በተገባደደው ዓመት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም አህጉራዊ አጀንዳዎችን ይዛ የመታገልና አፍሪካዊ ድምጽ ሆና የቀጠለችበት አመት ነበር፡፡ ለዚህም አብነቱ በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሔደው የፋይናንሻል ተቋማት ውይይት ላይ የታየው የኮንቬሽናል ወይም ትራክ ዋን ዲፕሎማሲ ነው፡፡ (መንግስት ከመንግስታት ጋር) ኢትዮጵያ በአለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ ሊኖራት ስለሚችለው ሚና እና እንደዚሁ የአፍሪካን መሠረታዊ ጉዳዮች ድምጽ ሆና በማስረዳት ረገድ አቅሟን ያሳየችበት አመት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካን ውክልና ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አንስቶ ኢትዮጵያ በየመድረኩ ድምጽ ስትሆን ቆይታለች፡፡ በዚህም የአፍሪካ ራሺያ ሰሚት ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተሳተፉበትና የሁለትዮሽ ግንኙነት የነበረበት ለመሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ከጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር በሁለትዮሽ የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራና በትብብር ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸው ተጠቃሽ የአመቱ ክዋኔ አካል ነው፡፡
በአህጉራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት ህግና መርህን በተከተለ መንገድ ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ሚና ባላቸው አጃንዳዎች ላይ ኢትዮጵያ የነበራት ተሳትፎ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሱዳን ያለው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ከኢጋድ አባል አገራት ጋር በቅንጅት ሰላምና ድርድር እንዲካሄድ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች፡፡
በብሪክስ 15ኛው አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የአባልነት ማመልከቻዋ ተቀባይነት ማግኘቷ ሌላኛው የ2015 ዓ.ም ሊታወስ የሚችል የዲፕሎማሲው ስኬት ነው፡፡
ለዘመናት ሲንከበለል የነበረው የህዝቦች የመደራጀት ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔና ምላሽ ያገኘበት አመት ነው፡፡ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሔደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማደራጀት ህዝበ ውሳኔ በ6 ዞኖችና በ5 ልዩ ወረዳዎች አዲስ 12ኛ የፌደራሉ አባል ክልል የተመሰረተበት ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ነባሩ የደቡብ ክልል ምንም አይነት ህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ሳያስፈልገው ሪፎርም በማድረግ ብቻ የማዕከላዊ ኢትዮጵ የተደራጀበት አመት ነው፡፡
“ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሔደው በአንድ ጀመበር 500 ሚሊዮን ችግን የመትከል ዘመቻ ሌላኛው የዓመቱ አበይት ክስተት ነበር፡፡ ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት መላው ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው የተሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፥ ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል የራሳችንን ሪከርድ ያሻሻልንበት አይረሴ አጋጣሚ ነበር፡፡
በ2015 ዓመት ኢኮኖሚው ዘርፍም በርከት ያሉ አበረታች የሚባሉ እንዲሁም በአሉታዊ መልኩ የሚገለጹ ክስተቶች ተስተናግደዋል።
በተለይ በግብርናው ዘርፍ የታየው መነቃቃትና አዲስ ጅማሬ ኢትዮጵያ የውስጥ ፍለጎቷን ሸፍና ስንዴን ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት ማድረግ መቻሏን ከብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ የስንዴ ኤክስፖርት ብሔራዊ ኮሚቴ የሰማነው በዚህ ባሳለፍነው አመት ነበር።
ብዙ ያስባለውና ከዚህ በፊት ባሉት ዓመታት ያልታየው የኑሮ ውድነት በዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከባድ ጫና አሳድሮ የቀጠለበት ነበር። ለበርካታ ሸቀጦች የዋጋ ንረት አይነተኛ ምክንያቱ ሁለተኛ አመቱን ለመያዝ እየተንደረደረ ያለው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ቢሆንም የዓለምን የገበያ ስርዓት ያናጋው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጠባሳ ቅሪቱ አሁንም ያላገገመ መሆኑን ነው።
በጥቅሉ ዓመቱ በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የተስተናገዱበት ቢሆንም 2016 የተሻለውን ይዞ ይመጣ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡ ሰላም!
አዘጋጅ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ