የአደረጃጀት ጥያቄ እንዲሳካ ህዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቀርባለሁ – አቶ እንዳሻው ጣሰው

ሀዋሳ: ጳጉሜ 05/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአደረጃጀት ጥያቄ እንዲሳካ ህዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ተናግረዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካና አስተዳደር መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ የሥራ ማስጀመሪያ የማጠቃለያ መርሀግብር በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል::

በመርሀግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ህዝቡ ጥያቄው እስኪመለስለትና ክልሉን መልሶ የማደራጀቱ ሂደት እስኪጠናቀቅ በትዕግስት በመጠበቅ ለዴሞክራሲ ግንባታ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል::

አዲስ ክልል እና አዲስ አደረጃጀት የመመስረታችን ፋይዳ የህዝባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥማት በቅርበት ሆነን ለመመለስ እንዲቻል ታስቦ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው የክልሉ አመራር በቅንነትና በታማኝነት ህዝቡን እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል::

የትውልድ ቀን በሚከበርበት እለት አዲሱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ማካሄዳችን አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብን እና ሀገራዊ አንድነት ላይ ይበልጥ በመሥራት ለትውልዱ ጠንካራ ሀገር ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል::

የአደረጃጀት ጥያቄ በመንግስትና ድርጅት ቁርጠኛ ውሳኔ እና በህዝባችን አስተዋይነትና ትዕግስት ምላሽ አግኝቶ ለዛሬዋ ቀን በመብቃታችን ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ያሉት ደግሞ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሀም መጫ ናቸው::

መላው ህዝባችን ላሳየው ትዕግስትና አጋርነት ምስጋና ይገባዋል ያሉ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላትም የህዝብ ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመለስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል::

ዘጋቢ: ማሬ ቃጦ