ለመላው የክልላችን ህዝቦች ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን – አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል

ለመላው የክልላችን ህዝቦች ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን – አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል

ሀዋሳ: ጷጉሜ 04/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለመላው የክልላችን ህዝቦች ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ተናግረዋል::

ዛሬ በቡታጅራ ከተማ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ክላስተር ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ተካሂዷል::

በመርሀግብሩ ላይ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ነስሩ ጀማል የቡታጅራ ከተማ የአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማዕከል ከተሞች መካከል አንዷ በመሆን የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ክላስተር መቀመጫ በመሆኗ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል::

ወደ ከተማ ለሚመጡ እንግዶች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ወደ ከተማዋ ለመጡና በቀጣይም ለሚመጡ እንግዶች መልካም ቆይታን ተመኝተዋል::

የህዝብን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ምላሽ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለፁት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው ከእንግዲህ የህዝብን ፍላጎ ለማርካት ለት ተቀን መሥራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል::

ህዝቡም አዎንታዊ ድጋፍ በማድረግ የከተማውንም ሆነ የክልሉን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል::

ፌዴራሊዝምን በተከተለ መልኩና የህብን አንድነት ይበልጥ በሚያስተሳስር መልኩ መንግስትና መሪው የብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ጥያቄ በመመለሱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ናቸው::

ክልሉ እምቅ አቅም ያለው ከመሆኑም በላይ የአብሮነትና የህዝብ የአንድነት እሴት ባለቤት የሆኑ ህዝቦች መገኛ ነው ብለዋል::

በክልሉ ያሉንን ጸጋዎች ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት ተጥሎብናል ያሉት አቶ ስንታየሁ ይህን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ክልሉን ለማበልፀግ አመራሩና ባለሙያው የሚተጋ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል::

ለመላውየክልሉ ህዝብ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለንም ብለዋል::

ዘጋቢ: ማሬ ቃጦ