የቡና ምርቱን ከማሳደግ ባለፈ ጥራቱን በማስጠበቅ በኩል በትኩረት እንደሚሰራ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ ተናገሩ

የቡና ምርቱን ከማሳደግ ባለፈ ጥራቱን በማስጠበቅ በኩል በትኩረት እንደሚሰራ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ ተናገሩ

በ2016 በጀት አመት ከዞኑ 33 ሺ ቶን በላይ የታጠበ እና ያልታጠበ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርናና አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ አስታውቋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ቡናን በዋናነት ከሚያመርቱ የደቡብ ምእራብ ክልል ዞኖች ተጠቃሽ ነው።

በዞኑ 154 ሺ ሄክታር መሬት በቡና ምርት የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 125 ሺ ሄክታር በላይም ምርት እንደሚሰጥ ነው የቤንች ሸኮ ዞን ግብርናና አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ሀላፊ አቶ መስፍን ጉባላ የተናገሩት።

በዚህም የክልሉን 50 ከመቶ ቡናን ከዞኑ እንደሚቀርብ ነው አቶ መስፍን የተናገሩት።

በ2016 በጀት አመትም የቡና አቅርቦት ጥራትን ለማረጋገጥ ከዞኑ እና ከወረዳ ከተወጣጡ የቡና ግብረሀይል ጋር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱም በተለይም ባለፉት አመታት ህገወጥ የቡና ግብይቶች መበራከታቸው የዞኑ ቡና ጥራት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በዚህም የዞኑ የቡና ምርት ጥራቱን ከመቀነስ ባለፈም የምርት መጠኑን እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በየደረጃው የተዋቀረ ግብረሀይልም ተግባሩን ጠንክሮ አለመስራት ተግዳሮትም እንደነበረ አውስተዋል።

በአዲሱ አመትም ይህ ድርጊት መደገም እንደሌለበት እና የዞኑን ቡና ጥራቱን በማስጠበቅ ወደ ማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዞኑ ካሉ 125 የእሸት እና የደረቅ ቡና ኢንዱስትሪዎች ከ33 ሺ 135 ቶን በላይ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል። የኸውም ከአርሶ አደሩ ባለፈም በዞኑ ካሉ 26 በኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲሁም ማህበራት እንደሚቀርብም ጠቁመዋል።

በግብረሀይሉ ውይይቱ ላይ የተገኙት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው ዞኑ በቡና ምርት በብዛት የሚታወቅ ቢሆንም ምርቱን በጥራት እና በብዛት ከማቅረብ አንጻር የሚገጥሙት ፈተናዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም ህገወጥ የቡና ዝውውር መኖር ጥራቱን ያልጠበቀ ቡና ወደ ገበያ መውጣት ፈተና መሆኑን ጠቁመው የቡና ግብረ ሀይሉ ተጠናክሮ በተገቢው የቁጥጥር ስራዎችን ከመስራት በዘለል በተለይም ጥራቱን በማስጠበቅ በኩል በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የወረዳ እና የዞን የቡና ግብረ ሀይል አባላትም በተለይም ወደታች በመውረድ በወረዳ ግብረ ሀይሎችን በማቋቋም ህገወጥ የቡና ዝውውርን በተገቢው ለመቆጣጠር የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የቡና ቁጥጥር ለማድረግ ቀደም ሲል የነበሩ ኬላዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረግ እንዳለበትም አስታውቀዋል።

የቡና ኢንዱስትሪዎችን በተገቢው የቅድመ ዝግጅት ተግባራቸውንም በመገምገም ጉድለት ያለባቸውን በማረም ወደስራ እንዲገብ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ቡና አቅራቢ ማህበራትንም አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ጥራት ያለው ቡና እንዲያቀርቡ ግብረሀይሉ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን