የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ተገለጸ

የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) መጪውን አዲስ አመት ተከትሎ በእርድ እንስሳትና በተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የ2016 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች እንደገለፁት የእርድ እንስሳት ግብይት ከአምናው ጋር ተቀራራቢ ቢሆንም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል ፡፡

ቀይ ሽንኩርት ቲማቲምና ነጭ ሽንኩርት በተመጣጣኝ ዋጋ ሲሸመቱ ቅቤ በኪሎ ከ750 እስከ 900 እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ በቂ የጤፍ ምርት ክምችት መኖሩን የሚገልፁት ነጋዴዎች ሠርገኛ ጤፍ በኪሎ 95 ብር ማኛ ጤፍ የተበጠረ 98 ብር እየሸጡ መሆናቸውን አስረድተው፥ ህብረተሰቡ አሉባልታ ወሬን ከመስማት  ይልቅ ተረጋግተው እንዲገበያዩ አስገንዝበዋል፡፡

የጂንካ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይግረም ላቀው እንደገለፁት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በበዓሉ እንዳይፈጠር ከነጋዴው ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው በህብረተሰቡ  ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥሩ ግብይቶችን ግብረ-ኃይሉ በማቋቋም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሁኔታዎችን ለንግድና ገበያ ልማት ጥቆማ እንዲሰጡ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርና ቅሬታ የሚፈጥሩ የግብይት ሂደቶችን ለመቅረፍ በግብረ ሀይል ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑም ተገልፀጿል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን