በአቅም ውስንነት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ህፃናትን ችግር ለመፍታት የሁሉም አካለት ርብርብ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአቅም ውስንነት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ህፃናትን ችግር በመፍታት ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲሄዱ ለማድረግ የሁሉም አካለት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ ፍኖተ ሰማይ ኢንተርናሽናል በጎ አድራጎት ማህበር ለ50 የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ምክትል ኃለፊ ወ/ሮ ስንታየሁ ምርከና እንዳሉት፥ የእኛ ልጆች የትምህርት ዕድል አግኝተው ሌሎች ደግሞ በአቅም ማነስ ምክንያት መቸገር የለባቸውም በሚል ሀሳብ ይህንን መልካም ተግባር እያደረጉ የሚገኙ የማህበሩ አባለት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በአቅም ውስንነት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲሄዱ ለማድረግ ሁሉም ህብረተሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጎ ማድረግ በዬትኛውም ኃይማኖት የሚደገፍ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ወ/ሮ ስንታየሁ አሳስባዋል።
የፍኖተ ሰማይ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪና የበጎ አድርጎት ማህበር መስራችና አስተባባሪ አቶ መልካሙ አሾሬ በበኩላቸው፥ የኃይማኖት አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት ለራሳቸው ካላቸው ጥቂት ነገሮች ከእኔ ለወገኔ በሚል ሀሳብ ለድጋፍ መነሳሳታቸውን ገልጻዋል።
የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች ከ60ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ በከተማ ለሚገኙ 50 ተማሪዎች በዕለቱ የደብተርና እስክሪብቶ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለ50 ተማሪዎች የደብተርና እስክሪብቶ እንዲሁም የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከትምህርት ቁሳቁስ በተጨማሪ በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሊስትሮ ዕቃዎችን በማግዛት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ጠቁመው፥ ለ20 አረጋውያን እናቶች ዱቄት፣ ዘይትና አልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዕለቱ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀው መሰል የአቅም ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖር ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ