በ2015 ዓ.ም በህብረተሰብ ተሳትፎ የታየውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል ለበለጠ ውጤታማነት እንደ ሚሠራ የኮንታ ዞን አስተዳደር
በዞኑ በማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ዘርፎች ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገብ መቻሉም ተገልጿል፡፡
የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ እንደገለጹት የኮንታ ዞን በዞን የመዋቅር ደረጃ ከተደራጀ ገና ሁለት ዓመት እያስቆጠረ ያለ ሲሆን ዞኑ በ3 ወረዳዎችና በ2 የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ነዋሪዎች በቅርበት የአገልግሎት ተደራሽነት ተረጋግጦ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
የዞኑን ነዋሪዎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተሠሩ መሆናቸውንም ያብራሩ ሲሆን በተለይም በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በተገቢው ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከተሞችን በማልማትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በተከናወነ ቅንጅታዊ ሥራ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
የመንግሥትን የወጪ ፍላጎት ለመሸፈን የታቀደውን ዕቅድ በማሳካት ያለጉድለት ወጪን ከመሸፈን ባለፈ የልማት ተግባራትን በተቻለ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል፡፡
ለህዝብ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ማከናወን መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በጤናና የትምህርት የልማት ተግባራት ላይ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀናጀት ለተማሪዎች መጽሐፍ ሕትመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ዞኑ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ የታደለ አካባቢ በመሆኑ ከቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የጨበራ ሎጂ ግንባታ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት መኖሩን ያስረዱት አስተዳዳሪው በተለይም በቅመማ ቅመምና በእንስሳት ሀብት እንዲሁም አሁን ላይ በቱሪዝም እና ሆቴል ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ለሚፈልጉ አልሚ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በ2015 ዓ.ም የታየው የህዝብ ተሳትፎና ድጋፍ በ2016 ዓ.ም እንዲታይ እንዲሁም ጽኑ ሰላም የሚረጋገጥበት፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው የሚመለሱበት ዓመት እንዲሆን በመመኘት ሁሉም በተሳተፈበት የሥራ መስክ የተጣለበትን ኃላፊነት በትጋት እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ ፡ መሣይ መሠለ- ከዋካ ቅርንጫፍ
More Stories
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ