ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ቃል የአገልጋይነት ቀንን የጎፋ ዞን አጠቃላይ አመራርና የመንግስት ሰራተኞች በፓናል ውይይት አከበሩ

ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ቃል የአገልጋይነት ቀንን የጎፋ ዞን አጠቃላይ አመራርና የመንግስት ሰራተኞች በፓናል ውይይት አከበሩ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ቃል የአገልጋይነት ቀንን የጎፋ ዞን አጠቃላይ አመራርና የመንግስት ሰራተኞች በፓናል ውይይት አከበሩ።

የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን በማጎልበትና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች የሚፈቱበት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ በመወያየት የአገልጋይነት ቀን ተከብሯል።

የጎፋ ዞን ፐቪልክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አካሉ አምቦ አመራሩና ባለሙያው ህብረተሰቡን ለማገልገል በተመደበበት ዘርፍ በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ህብረተሰቡን በአግባቡና በሚፈለገው ልክ ለማገልገል ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተገልጋዩን እርካታ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።

የጎፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ማሩፋ መኩሪያ በበኩላቸው የመንግስት ሰራተኞች በተሰማሩበት የሙያ መስክና ኃላፊነት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ከ20 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች መኖራቸውን የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው የውይይቱ ተሳታፊዎች አገርን ከማገልገል በላይ ክብር አለመኖሩን ተረድተው ህዝብን በቅንነት ማገልገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

አገልጋይነት ጊዜና እውቀትን በለጋስነት መስጠት መሆኑን ያስረዱት ዋና አስተዳዳሪው ዝቅ ብሎ ማገልገል ከፍታን የሚያስገኝ መሆኑንም  ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአገልጋይነት ስሜትን በመላበስ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝቡ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚታዩ ብልሹ አሰራሮች በጋራ ለመመከት ቃላችንን የሚያድሱበት ዕለት መሆኑንም አስተያዬት ሰጪዎቹ አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን