ሀዋሳ፡ ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ደስታ ደምሴ ለዳውሮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የ”ቶክ-በኣ” በኣል በዳውሮ ብሔረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ የመጣ የዘመን መለወጫ ሲሆን አመቱን ሙሉ ወጥቶ ወርዶ የተሻለ በማምረት በአዲስ አመት ዋዜማ ሰውም ሆነ የቤት እንስሳት ጠግበው እንዲያድሩና ቤት ውስጥ ያሉ የሽክላ እቃዎች በውሃ ተሞልተውና ተከድነው እንዲቀመጡ የሚያስተምር ነው በማለት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ደስታ ደምሴ ገልጸዋል።
በዕለቱ በአሮጌው አመት የነበረ መጥፎ ነገር ሁሉ ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሻገር ሽማግሌዎች ፀሎት የሚያደርጉበትም ነው ብለዋል።
የጨረቃ እንቅስቃሴን መሰረት በማድረግ የሚከበረው የዳውሮ ብሔረሰብ ዘመን የመቁጠርና ወቅቶችንም የመለየት እውቀት የበለጠ ለምቶና ተጠንቶ ለሀገር እሴትነት ሊውል የሚገባ መሆኑንም አመላክተዋል።
የዳውሮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ለዞኑ ማህበረሰብና እንደሀገርም የሚሆኑ በርካታ እሴቶች ያሉት በመሆኑ ይህን በዓል አጠናክሮ ለማስቀጠል የዞኑ አስተዳደርም ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል።
በበዓሉ እለት የቀጣይ አመቱን የሥራ ተግባራትን በሚመለከት የአባቶች ምክር፣ ለአካባቢው እና ሀገር ፀሎት የሚደረግበትና የብሔረሰቡ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችንም ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥርበት መሆኑን ዋና አስተዳደሩ ተናግረዋል።
በዓሉ የህዝብ መሠረት ያለው በመሆኑ ይህንን በማጥናት፣ በማሳወቅና ለትልድ ለማሸጋገር የዘርፉ ተቋማት የበኩላቸውን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አንስተዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደምሴ እንኳን ለዳውሮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ቶክበኣ በዓል በሠላም አደረሳችሁ በማለት አዲሱ ዓመት የሥራ፣ የበረከት፣ የመተባበር ፣ የሠላምና የብልጽግና እንዲሆንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ