ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግስት ሰራተኞች የሕዝብ አገልጋይ እንደመሆናቸዉ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ከብልሹ አሰራር በጸዳ ሁኔታ ማከናወን እንዳለባቸው ተገለጸ።
የ2015 ዓ.ም ጳጉሜን አንድ “የአገልጋይነት ቀን”ን በማስመልከት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አመራሮችና ሠራተኞች በቦንጋ ከተማ አክብረዋል።
የደቡብ ምዕራብ እትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አመራሮችና ሠራተኞች እለቱን በማስመልከት በቦንጋ ከተማ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።
በእለቱ አገልግሎትን በቅርበት ለመስጠትና ሂደቱንም ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት የክልሉ ፐብልክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት አዳሮ ናቸው።
ለአገልግሎት ጥራት መጓደል በምክንያትነት የሚነሱ ብልሹ አሰራሮችን ለማጥራት በተሰሩ ሥራዎች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገስጉትን በመለየት በተወሰደ ርምጃ ከ84 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስት ሀብት ከብክነት ማትረፍ ተችላል ብለዋል።
በተመደቡበት የሥራ ዘርፍና ኃላፊነት ላይ ተገቢውን አገልግሎት በቅንነት የሚሰጡ የመኖራቸውን ያህል ግዴታቸውን የሚዘነጉና ባልተገባ ቦታ ጊዜ የሚያጠፉ ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆኑ የገለጹት ኃላፊው መጪዉ አዲስ አመት ሁሉም የመንግስት ሠራተኞች ለዉጤታማ አገልግሎት የሚዘጋጁበትና በአፈጻጸማቸው እውቅና የሚሰጥበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የእድገት ማማ ላይ የደረሱ ሀገራት መሰረታቸዉ ጠንካራ የሲቪል ስርቪስ ተቋማትን መገንባት በመቻላቸዉ ነዉ ያሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ሕዝብን በቅንነት ማገልገል ደግሞ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበትን በማይፈጅ ሁኔታ ዉጤታማ ሥራን ማከናወን እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ከቅጥርና ምደባ ጋር የተያያዙ የአሰራር ሥርኣት፣ ደንብና መመሪያ ከመተግበር አኳያና የኑሮ ዉድነትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዉ ምላሽና ማብራሪ ተሰጥቶባቸዋል።
የክልሉ መንግስት የሰራተኖችን ጥቅማጥቅምና ሌሎች የመብት ጥቄዎችን በአግባቡ በማስተናገድ የድርሻዉን እንደሚወጣ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ቅርንጫፍ ጣቢያችን
More Stories
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ